በምዕራብ ጎንደር ዞን ነጋዴ ባህር እና ጭልጋ ቁጥር 1 ወረዳ በደረሱ ሁለት ድንገተኛ የመኪና አደጋዎች በታጣቂዎች በጥይት የተገደለውን ሾፌር ጨምሮ የ6 ሰዎች ህይወት ማለፉን የአካባቢው ነዋሪ…

በምዕራብ ጎንደር ዞን ነጋዴ ባህር እና ጭልጋ ቁጥር 1 ወረዳ በደረሱ ሁለት ድንገተኛ የመኪና አደጋዎች በታጣቂዎች በጥይት የተገደለውን ሾፌር ጨምሮ የ6 ሰዎች ህይወት ማለፉን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ጥቅምት 22 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ በምዕራብ ጎንደር ዞን ነጋዴ ባህር እና ጭልጋ ቁጥር 1 ወረዳ ትናንት ጥቅምት 21 ቀን 2013 ዓ.ም በደረሱ ሁለት ድንገተኛ የመኪና አደጋዎች በታጣቂዎች በጥይት የተገደለውን ሾፌር ጨምሮ የ6 ሰዎች ህይወት ማለፉን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል። ጥቅምት 21 ቀን ከሰዓት በኋላ በምዕራብ ጎንደር ዞን አዳኝ አገር ጫቆ ወረዳ በነጋዴ ባህር ከተማ በማንነታቸው የቅማንት ተወላጅ የሆኑ አንዲት እናት ለገበያ ከገጠር እንደመጡ በአባዱላ መኪና በድንገት መገጨታቸውንና ሾፌሩም ወዲያውኑ ስለማምለጡ ምንጮች ተናግረዋል። የተገጩት እናትም ሪፈር በመባላቸው የአዳኝ አገር ጫቆ ወረዳ የአምቡላንስ ሾፌር በተሰጠው ትዕዛዝ መሰረት ወደ ገንዳ ውሀ ከተማ እንደወስዳቸው ህይወታቸው አልፏል። በመሆኑም አስከሬን ጭኖ ወደ ነጋዴ ባህር ከተማ ሲመለስም በቅርብ ርቀት ወደ ሚገኘው አቸራ ወደተባለው የሟች መኖሪያ አካባቢ ከሟች ልጆች ጋር ሆኖ አስከሬኑን ወስዷል። መንገድ ላይ በርካታ አስከሬን ተቀባዮች ተገኝተው አስከሬን እያወረዱ ባሉበት ሰዓት ከጎንደር ወደ መተማ አቅጣጫ የሚጓዝና ከአምቡላንሱ በስተኋላ በኩል በፍጥነት የመጣው ኦባማ ከውጭ ያሉ ሰዎችን ሲገጭና ወደ ጎን ሲገለበጥ ማስተዋሉን የአምቡላንስ ሾፌሩ ተናግሯል። አደጋው የተከሰተው ከቀኑ 11 ሰዓት አካባቢ መሆኑን የገለፀው የአምቡላንስ ሾፌሩ በወቅቱ የደረሰውን ድንገተኛ አደጋና ተኩስ ተከትሎ ተደናግጨም ስለነበር ምን ያህል ሰው እንደተጎዳ ለማወቅ አልቻልኩም ነው ያለው። የኦባማ ሾፌሩን ከኋላው የሚያሳድደው አካል ነበር ወይ? ለተባለው ሲመልስ አላወኩም ነው ያለው። ሾፌሩ ሲቀጥል ምንም እንኳ ተከፍቶ በነበረው የአምቡላንሱ በር ላይ መጠነኛ ጉዳት ቢደርስበትም በቦታው በነበሩ ሁለት ሰዎች ትብብር መከላከያ ወዳለበት ደርሼ ወታደሮች ባደረጉልኝ እገዛ በሰላም ወደ ቤቴ ተመልሻለሁ ብሏል። በፍጥነት ሲያሽከረክር ስለነበር ምንአልባትም ሾፌሩ ለመቆጣጠር ተቸግሮ ይሆናል፤ በተጨማሪም በአካባቢው በተለያዩ ጊዜያት ሾፌር ስለሚታገትና በርካታ ሰዎችም ከበው ሲመለከት በድንጋጤ በፍጥነት አቋርጦ ለማለፍ ፈልጎ ሊሆን ይችላል ሲልም አስተያየት ሰጥቷል። ሌላኛው የአካባቢው ምንጫችን ደግሞ ከጎንደር ወደ መተማ የሚሄደው የኦባማ መኪና ተገልብጦ በደረሰ አደጋ አስከሬን በመቀበል ላይ ከነበሩት በርካታ የቅማንት ተወላጆዎች መካከል 4ቱ ተገጭተው ወዲያውኑ ሲሞቱ፣ የቆሰሉም ስለመኖራቸው ገልጧል፤ ሾፌሩም በቅማንት ታጣቂዎች ወዲያውኑ በጥይት ስለመገደሉ ነው የተናገረው። የቅማንት ታጣቂዎች መንገድ ላይ ጠብቀው እንዲቆም ሲጠይቁት በፍጥነት በማሽከርከር ለማምለጥ ሲሞክር ነው አደጋው የተከሰተው ሲልም አክሏል። የመጀመሪያው አደጋ እንደተከሰተ ለፀጥታ አካላት ስምሪት ተሰጥቶ በአካባቢው ጥበቃ ማድረግ አስፈላጊ እንደነበር የገለፀው የመረጃ ምንጫችን አሁንም መንግስት በፓትሮል ጥበቃውንና ቅኝቱን እንዲያጠናክር አሳስቧል። በአጠቃላይ የደረሰን መረጃ እንዳመለከተው በነጋዴ ባህርና ጭልጋ ቁጥር 1 ወረዳ በደረሱ ሁለት የመኪና አደጋዎች በታጣቂዎች በጥይት የተገደለውን ሾፌር ጨምሮ የ6 ሰዎች ህይወት አልፏል። በኦባማው ውስጥ ከሾፌሩ ውጭ ሌላ የተሳፈረ ተጓዥ ስለመኖሩ ምንጮች ማረጋገጥ አልቻሉም። የወረዳውን የፖሊስ አዛዥ አድራሻ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው ባለመሳካቱ ስለደረሰው አደጋና የሟቾችን ቁጥር በተመለከተ ከተቋሙ ለማረጋገጥ አልተቻለም። የአማራ ሚዲያ ማዕከል በደረሰው አሳዛኝ አደጋና ግድያ የተሰማውን ሀዘን በመግለፅ ነፍስ ይማር እያለ ለሟች ቤተሰቦች መፅናናትን፣በአደጋው ለቆሰሉት ደግሞ ፈጣን ማገገምን ይመኛል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply