በምዕራብ ጎንደር ዞን አዳኝ አገር ጫቆ ወረዳ በሻሃርዳ ቀበሌ ከንግድ ግብር አከፋፈል ጋር ተያይዞ ከ10 በላይ ነጋዴዎች አላግባብ ታስረውብናል ሲሉ ቤተሰቦች ቅሬታ አቀረቡ። አማራ ሚዲያ ማዕከ…

በምዕራብ ጎንደር ዞን አዳኝ አገር ጫቆ ወረዳ በሻሃርዳ ቀበሌ ከንግድ ግብር አከፋፈል ጋር ተያይዞ ከ10 በላይ ነጋዴዎች አላግባብ ታስረውብናል ሲሉ ቤተሰቦች ቅሬታ አቀረቡ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ታህሳስ 28 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ ከምዕራብ ጎንደር ዞን አዳኝ አገር ጫቆ ወረዳ ከሻሃርዳ ቀበሌ ለአሚማ የደረሰው መረጃ እንዳመለከተው ከንግድ ግብር አከፋፈል ጋር በተያያዘ በቀበሌው ከ10 በላይ ሰዎች ታስረዋል። ቅሬታ አቅራቢዎቹ እንደገለፁት በሻሃርዳ ቀበሌ ከንግድ ግብር አከፋፈል ጋር ተያይዞ ከ10 በላይ ነጋዴዎች አላግባብ ታስረዋል። በሻሃርዳ ቀበሌ በንግድ እና በእርሻ እንቅስቃሴ ለመሰማራት የንግድ ፍቃድ ስንጠይቅ ፍቃድ አይሰጡንም፤ ኑሮአችን ከእጅ ወደ አፍ ሆኖ እያለ የግብር ክፍያ ህግን ያልተከተለ ያለውንና የሌለውን ያላመዛዘነ ሱሪ ባንገቴ የሆነ የግብር አከፋፈልን በመቃወማቸው ነጋዴዎች ታስረውብናል ብለዋል። ያለአቅማችን ግብር ለመክፈል ይቸግረናል በማለታቸው ከታሰሩት የሻሃርዳ ቀበሌ ነጋዴዎች መካከልም ዲያቆን አጉማስ ጨቅሌ፣ አቶ ደሣለኝ፣ አቶ አለልኝ መንግስቴ ከእነ ባለቤታቸው፣ አቶ ኪሮሥ፣አቶ ደጉ አላምረው፣ ነጋ ተሥፋሁን በማለት ቁጥራቸው እስከ 11 መድረሱን አመልክተዋል። ስለጉዳዩ ያነጋገርናቸው በአዳኝ አገር ጫቆ ወረዳ የሻሃርዳ ቀበሌ ሊቀ መንበር አቶ ሽባባው አቆየ ግብር መክፈል የዜግነት ግዴታ ነው፤ በተደጋጋሚ እንዲከፍሉ ተጠይቀው አልከፍልም በማለት ያንገራገሩ ሰዎች መታሰራቸውን ገልፀዋል። በአንድ ቤት ያሉ አስመስሎ አቶ አለልኝ መንግስቴ ከእነ ባለቤታቸው ታሰሩ የተባለው ስህተት ነው፤ መታሰራቸው እውነት ቢሆንም ሁለቱም የተለያዩ እና በየራሳቸው የግል ስራ ተሰማርተው የሚገኙ ናቸው፤ የተጠየቁትም በየግላቸው ለሰሩበት ነው ሲሉ አስተባብለዋል። የንግድ ግብሩ የሚጣለው ከእነሱ በባለሙያዎች ተወስዶ እንጅ እንዲሁ የሚወሰን አይደለም፤ ከፍለው ቅሬታ ማስገባት ይችላሉ እንጅ አንከፍልም የሚል አካሄድ አይጠቅመንም ብለዋል። በከፊል እንኳ ከፍለው ቅሬታቸውን የሚያሰሙበት ሁኔታ እንዲፈጠር ከሚመለከተው የግብር አስከፋይ አካል ጋር እንነጋገራለን ብለዋል_አቶ ሽባባው አቆየ። ከግብር አስከፋዩ መ/ቤት ገቢዎች ጽ/ቤትም የሚመለከተውን አካል ለማግኘት ያደረግነው ጥረት የሚጠራ ስልካቸው ባለመነሳቱ ለጊዜው ሀሳባቸውን ለማካተት አልተቻለም።

Source: Link to the Post

Leave a Reply