
በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ቀይ ቀበሮዎችን ለመከታተልና መረጃ ለመሰብሰብ የሚያግዝ «ፖላር» የተሰኘ ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ ዋለ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ መጋቢት 21 ቀን 2015 ዓ/ም … አዲስ አበባ ሸዋ በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የቀይ ቀበሮዎችን ብዝሃ ሕይወት ለመጠበቅና ለመከታተል የሚያግዝ «ፖላር» የተሰኘ ቴክኖሎጂን ጥቅም ላይ ማዋል መጀመሩን የፓርኩ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡ በጽሕፈት ቤቱ የቀይ ቀበሮዎች ጥበቃ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ጌታቸው አሰፋ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ቴክኖሎጂው በፓርኩ ያሉ ቀይ ቀበሮዎችን የአኗኗርና የጤና ሁኔታ እንዲሁም ሥነ-ተዋልዶና እንቅስቃሴያቸውን ለመከታተል የሚያግዝ ነው። ቴክኖሎጂው ከዚህ ቀደም በፓርኩ ስለቀይ ቀበሮዎች መረጃ ለማሰባሰብ በባለሙያዎች ይካሄድ የነበረውን አድካሚ የእግር ጉዞ በማስቀረት በቴክኖሎጂ የታገዘ ሳይንሳዊ መረጃ ለማሰባሰብ እንደሚያስችል አስረድተዋል። አቶ ጌታቸው እንዳሉት ቴክኖሎጂው በቀይ ቀበሮዎች አንገት ላይ የሚታሰር ሲሆን በሳተላይት አማካኝነት መረጃዎችን ለመሰብሰብ የሚያስችል ነው። ባለፉት ሦስት ሳምንታት በተደረገ እንቅስቃሴ በአራት ቀይ ቀበሮዎች አንገት ላይ ቴክኖሎጂው ታስሮ ሥራው መጀመሩንም ተናግረዋል። በቀይ ቀበሮዎቹ አንገት ላይ የተገጠመው ቴክኖሎጂ በአንድ ላይ የሚኖሩ እስከ 40 የሚደርሱ የቀይ ቀበሮ የቤተሰብ አባላትን ለመከታተል እንደሚረዳም ገልጸዋል። ቴክኖሎጂው በፓርኩ ከተዘጋጀው የመረጃ ቋት ሥርዓት ጋር በመገናኘት የቀበሮዎቹን ደህንነትና ያሉበትን ቦታ ጭምር በየዕለቱ ለመከታተልና መረጃዎችን ለማደራጀት የሚያግዝ መሆኑንም አብራርተዋል። እንደ አስተባባሪው ገለጻ ቴክኖሎጂው የተገጠመለት ቀይ ቀበሮ በቀን ምን ያህል ኪሎ ሜትር እንደተጓዘና የት ቦታ እንደሚገኝ እንዲሁም በሕይወት ስለመኖሩና ሲሞትም የት ቦታ ሞቶ እንዳለ መረጃ የሚጠቁም ነው። በቀጣይ ሳምንታትም በተጨማሪ ሁለት ቀይ ቀበሮዎች ላይ ቴክኖሎጂው እንደሚገጠም ገልጸው፣ መሣሪያው ለተገጠመላቸው ቀይ ቀበሮዎች የእብድ ውሻ በሽታ መከላከያ ክትባት መሰጠቱንም አመልክተዋል። አቶ ጌታቸው እንዳሉት አዲሱ ቴክኖሎጂ ከዚህ ቀደም በባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በሚገኙ ቀይ ቀበሮዎች ላይ ተሞክሮ ባስገኘው ውጤት መነሻነት በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ ተደርጓል። «ቴክኖሎጂው ቀይ ቀበሮዎቹ ያሉበትን ቦታ መጠቆሙ ከዚህ ቀደም ጎብኚዎች ቀበሮዎቹን ፈልጎ ለማየት የሚደርስባቸውን እንግልት ያስቀራል» ያሉት ደግሞ የፓርኩ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዛናው ከፍያለው ናቸው። ባለፉት ዓመታት በፓርኩ ክልል ውስጥ ተግባራዊ የተደረገው የልቅ ግጦሽ ቅነሳ ስትራቴጂ በውሾች አማካኝነት ወደ ቀይ ቀበሮዎች ይተላለፍ የነበረውን የእብድ ውሻ በሽታ ስርጭት መቀነስ እንዳስቻለም ተናግረዋል። ኃላፊው እንዳሉት በፓርኩ ክልል ዋነኛ የቀይ ቀበሮዎች መኖሪያና መገኛ ሥፍራዎች መካከል ግጭ፣ አይና ሜዳ፣ ጨነቅ፣ ሰባት ምንጭ እና ቧሂት ይጠቀሳሉ። በአሁኑ ወቅት በፓርኩ ውስጥ ቁጥራቸው 90 የሚደርሱ ቀይ ቀበሮዎች የሚገኙ ሲሆን ከ20 ዓመት በፊት ቁጥራቸው 20 ብቻ እንደነበር አስታውሰዋል። በአውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር በ1978 በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም የተፈጥሮ ቅርስነት የተመዘገበው የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ 412 ስኩየር ኪሎ ሜትር ስፋት አለው። የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙትን ዋልያ፣ ቀይ ቀበሮ እና ጭላዳ ዝንጀሮን ጨምሮ የሌሎች ብርቅዬ የዱር እንስሳትና አዕዋፋት መገኛ ስፍራ መሆኑ የሚታወቅ ነው። ዘገባው_የአማራ ኮሚዩኒኬሽን ነው።
Source: Link to the Post