በሰሜን አቸፈር ወረዳ የቁንዝላ እና የአካባቢው ነዋሪዎች ለወራት የተቋረጠው የመብራት አገልግሎት እንዲስተካከልላቸው በተደጋጋሚ ላቀረቡት ጥያቄ በጎ እና አፋጣኝ ምላሽ ባለመሰጠቱ ለሁለተኛ ቀን…

በሰሜን አቸፈር ወረዳ የቁንዝላ እና የአካባቢው ነዋሪዎች ለወራት የተቋረጠው የመብራት አገልግሎት እንዲስተካከልላቸው በተደጋጋሚ ላቀረቡት ጥያቄ በጎ እና አፋጣኝ ምላሽ ባለመሰጠቱ ለሁለተኛ ቀን መንገድ መዝጋታቸውን አስታወቁ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ የካቲት 21 ቀን 2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ሸዋ በምዕራብ ጎጃም ዞን ሰሜን አቸፈር ወረዳ የቁንዝላ እና አካባቢው ነዋሪዎች ከአማራ ሚዲያ ማዕከል (አሚማ) ጋር ቆይታ ያደረጉ ነዋሪዎች እንደገለጹት ለወራት የተቋረጠው የመብራት አገልግሎት እንዲስተካከልላቸው በተደጋጋሚ የተለያዩ ተቋማትን በር ያንኳኩ ቢሆንም በጎ እና አፋጣኝ ምላሽ ለማግኘት አልቻልንም ብለዋል። ያቀረብነው መሰረታዊ የሆነ የተጠቃሚነት የመብት ጥያቄ መሆኑ እየታወቀ መብራት ኃይልን ጨምሮ ሌሎች ተቋማት በኃይል በማስፈራራት እና ጫና በማድረግ ጥያቄያችን ሲያዳፍኑ ቆይተዋል ነው ያሉት። በዚህም ምክንያት ዛሬ ለ2ተኛ ቀን መንገድ ወደ መዝጋት የሄድነው ምላሽ የሚሰጠን አካል ለማግኘት በሚል ነው የሚሉት የቁንዝላ እና የአካባቢው ነዋሪዎች ይህን የህዝብ ጥያቄ በኃይል ለማዳፈን የሚሞከር ከሆነ ግን ትግላችን አጠናክረን እንደምንቀጥል እወቁት ሲሉም አስጠንቅቀዋል። ሰሜን እና ደቡብ ሱዳን እንዲሁም ጅቡቲን ተጠቃሚ እያደረገው ያለው መብራት ኃይል የሃይል ማመንጫው ጣና በለስ የተቋቋመበትን አካባቢ ተጠቃሚ አለማድረጉ በእጅጉ አሳዛኝ ነው ብለውታል ነዋሪዎቹ። ችግሩ የመብራት ብቻ ሳይሆን ሁለንተናዊ ነው የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎች መብራት ባለመኖሩ ውሃ የለም፣ የስራ እድል የለም፣ ሁሉም ነገር ያቆመ በመሆኑ አስቸኳይ ምላሽ ሊሰጠን ይገባል በሚል ፍጹም ሰላማዊ የሆነ ጥያቄ በማቅረብ ላይ እንገኛለን ብለዋል። ቁንዝላ ላይ መንገድ መዘጋቱን ተከትሎ በተመሳሳይ መስመር ያሉት ባህር ዳር፣ ቋራ ደለጎ፣ ጎንደር፣ እንዲሁም ሻውራ እና ዱርቤቴም መስመሩ በመዘጋቱ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተሽከርካሪዎች አሁን ላይ ቆመው ይገኛሉ፤ ከፍተኛ የሆነ መስተጓጎል እየታዬ ነው ተብሏል። በቁንዝላ ነዋሪዎች እንደሚሉት አሁን ላይ የሚሰሩ ተቋማት ት/ቤት፣ ጤና ጣቢያና ከዱር ቤቴ ደለጎ የቻይና መንገድ ስራ ፕሮጀክት ናቸው። ባንክን ጨምሮ ሌሎች ተቋማት በመብራት ችግር ስራ ላይ አይደሉም፤ የግል ተቋማትም በመዝጋት ተቃውሞ ላይ ናቸው ብለዋል። የየካቲት 20/2015 እንቅስቃሴን ተከትሎ ከወረዳ፣ ከዞንም ሆነ ከክልል አመራር መጥቶ ማነጋገር ሲገባው ከወረዳ ሚሊሻ የተላከበት መንገድም የነዋሪዎችን ጥያቄ በኃይል ለመመለስ የታሰበ ነው በሚል አስቆጥቷል። ስለጉዳዩ አሚማ ያነጋገራቸው የጣና በለስ ኃይል ማመንጫ ዋና ስራ አስኪሂያጅ አቶ ቢምረው ዳኘው ጥያቄው ትክክል እና ተቀባይነት ያለው መሆኑን እንደሚጋሩት በመግለጽ ችግሩም የቆዬ ስለመሆኑ ተናግረዋል። ለሶስት ወረዳዎች አገልግሎት የሚሰጠው ትራንስፎርመር አንድ አይሉ ሁለት ጊዜ በመቃጠሉ ችግሩ አሁንም አልተፈታም ብለዋል። ጉዳዩ ለሚመለከተው አካል ደርሶ ምላሽ ለመስጠት በሂደት ላይ ስለመሆናቸውና እቃውም ከውጭ ስለሚመጣ ጊዜም እየወሰደ ስለመሆኑ ተናግረዋል። እኛ በዋናነት የሚመለከተን የጣና በለስ ኃይል የማመንጨቱን ስራ ላይ ነው ሲሉም አቶ ቢምረው ምላሽ ሰጥተዋል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply