በሰሜን ወሎ ራያ ቆቦ የተሳካ ሰላማዊ ሰልፍ ሲደረግ በአንጻሩ በባህርዳር ከተማ የተደረገው እንቅስቃሴ በፀጥታ አካላት ብተና እና ክልከላ ገጥሞታል፤ የተደበደቡም አሉ ሲሉ የተቃውሞ ሰልፉ ተሳታ…

በሰሜን ወሎ ራያ ቆቦ የተሳካ ሰላማዊ ሰልፍ ሲደረግ በአንጻሩ በባህርዳር ከተማ የተደረገው እንቅስቃሴ በፀጥታ አካላት ብተና እና ክልከላ ገጥሞታል፤ የተደበደቡም አሉ ሲሉ የተቃውሞ ሰልፉ ተሳታፊዎች ተናገሩ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ጥቅምት 18 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ አብን ቀደም ሲል ጥቅምት 18 እና ጥቅምት 22 ቀን 2013 ዓ.ም በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞችና በአዲስ አበባ ሰላማዊ ሰልፍ መጥራቱ እና በኋላም ተፈፀመበትን ክልከላና አፈና ተከትሎም ሰልፉን ለማስተባበር እንደማይችል መግለፁ ይታወሳል። ይሁን እንጅ በአማራ ላይ የሚፈፀመውን የዘር ማጥፋት ወንጀል የሚያወግዘው ሰልፍ ከድርጅት በላይ ነው፣ የመላ አማራ ህዝብ ጥያቄ ነው በማለት በዛሬው ዕለት ሰላማዊ ሰልፍ ከተደረገባቸው አካባቢዎች መካከል አንዱ በሰሜን ወሎ ዞን የሚገኘው ራያ ቆቦ ነው። በራያ ቆቦ የተደረገው ህዝባዊ ሰልፍ በርካታ መልዕክቶች የተላለፉበት፣ሰላማዊና ስኬታማ እንደነበር የገለፀው የራያ ቆቦ ነዋሪና የሰልፉ ተሳታፊ ወጣት አበበ ፈንታሁን ነው። ወጣት አበበ ከአማራ ሚዲያ ማዕከል ጋር በነበረው ቆይታ ሰልፉ በአማራ ህዝብ ላይ የሚፈፀመውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ያወገዘበትና ማስጠንቀቂያም የሰጠበት ጭምር እንደሆነ አስታውቋል። በተመሳሳይ በባህር ዳር ከተማ ዛሬ ጥቅምት 18 ቀን 2013 ዓ.ም ከማለዳው ጀምሮ በአማራ ላይ የሚፈፀመው የዘር ማጥፋት ወንጀል እንዲቆም በሰልፉ በተሳተፉና ድምጻቸውን ባሰሙ ነዋሪዎች ላይ በአድማ ብተና ሀይሎች አማካኝነት ክልከላና ድብደባ የተፈፀመባቸው መሆኑ ተገልጧል። ከፍተኛ ቁጥር ያለው የፀጥታ ሀይል ስምሪት ተደርጎ በሰልፉ ላይ የነበሩ ወጣቶችንና ሰላማዊ ነዋሪውን ህዝብ ጭምር የማሸበር ሁኔታዎች እንደነበሩ ተገልጧል። በአድማ በታኞች አማካኝነት በአካላቸው ላይ ድብደባ ከተፈፀመባቸው መካከልም ወጣት ምስጋናው በለጠ/ምስጋናው ዘጊዮንን አነጋግረናል። የህግ ባለሙያ የሆነው ወጣት ምስጋናው በፀጥታ አካላት የተፈፀመው ድርጊት አሳፋሪና አሳዛኝ መሆኑን ጠቅሶ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ህዝቡ ጠንክረው እንዲታገሉ አሳስቧል። ባህር ዳርን ጨምሮ በምዕራብ ጎጃም ዞን በቡሬ፣በፍኖተ ሰላም፣በዱርቤቴ፣በሰሜንና ደቡብ ሜጫ እንዲሁም በሌሎችም አካባቢዎች የነበረውን የሰልፍ ሙከራ ተከትሎ በአብን አመራሮች፣አባላትና ደጋፊዎች ስለተፈፀመው መረጃ ያካፈሉን በምዕራብ ጎጃም ዞን የአብን ም/ሰብሳቢ አቶ አሸናፊ አካሉ ናቸው። ብአዴን ምንጊዜም ቢሆን አይለወጤ መሆኑን የታየበት እንቅስቃሴ መሆኑን ጠቅሰው ቀጣይ በፓርቲያቸው የሚሰጠውን አቅጣጫ መሰረት በማድረግ ትግሉን ከፍ ወዳለ ደረጃ እናሸጋግራለን ብለዋል። የአማራ ሚዲያ ማዕከል አጠቃላይ ስለነበረው የተቃውሞ ሰልፍ እንቅስቃሴውንና በስርዓቱ የፀጥታ አካላት በኩል ሲፈፀም የነበረውን ወከባ በተመለከተም አክቲቪስት ቶማስ ጀጃውን አነጋግሯል። ሰልፉ የአብን ብቻ ሳይሆን የመላ አማራ እና የሰው ልጆች ሁሉ የሰብአዊነት ጥያቄ የሚስተናገድበት መሆኑን ጠቅሶ ሰፋ ያሉ መረጃዎችንና እይታውን አጋርቶናል። በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውሀ ከተማ ምንም እንኳ ሰልፍ ባይደረግም አስፋው ፍስሀ የተባለ የአብን አባል በአስተባባሪነትና በፌስ ቡክ ገፅህ ቀስቃሽ ሀሳብ አስተናግደሀል፤ እረፍ በሚል ወደ ልዩ ሀይል ካምፕ ተወስዷል። በመቀጥልም ወደ ሰላምና ደህንነት ጽ/ቤት እንዲሁም ወደ ገንዳ ውሀ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ ተወስዶ ቀስቃሽ ነገሮችን ከመፃፍ እንዲቆጠብ በሚል ፈርሞ እንዲወጣ መደረጉን አረጋግጠናል። በተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች ተመሳሳይ ወከባዎች ይፈፀሙና በስርዓቱ ሰዎች ዘንድም መደናገጦች እንደነበሩ ለማወቅ ተችሏል። ከአበበ ፈንታሁን፣ከምስጋናው ዘጊዮን፣ከአሸናፊ አካሉ፣ከአስፋው ፍስሀ እና ከአክቲቪስት ቶማስ ጀጃው ጋር ያደረግነውን ቆይታ በአማራ ሚዲያ ማዕከል ይጠብቁ።

Source: Link to the Post

Leave a Reply