በሰሜን ጦርነት ሳቢያ የተጎዳው ታሪካዊው አል ነጃሺ መስጂድ ጥገና በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ይጀመራል 

ሐሙስ ግንቦት 15 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ እና ቱርክ መንግስታት በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የተጎዳውን ታሪካዊው የአል ነጃሺ መስጂድ ለመጠገን ተስማሙ።

አዲስ ማለዳ ከቱሪዝም ቢሮ ባገኘችው መረጃ የኢትዮጵያ እና የቱርክ ባለስልጣናት በአገራቱ ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠውን የአል-ነጃሺ መስጂድ እድሳት ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ይፋ አድርገዋል።

በኢትዮጵያ የቱርኪዬ ሪፐብሊክ አምባሳደር ቤርክ ባራን እና የቱርኪዬ የትብብር እና ድጋፍ ኤጀንሲ አስተባባሪ ኤንቨር ሬሱሎጉላሪ ከቱሪዝም ሚኒስቴር አመራሮች ጋር የፕሮጀክቱን የመጨረሻ እርምጃዎች በተመለከተ ተወያይተዋል።

“በሚቀጥሉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ” የጥገና ስራውን መጀመር እንዲሁም የቦታውን ይፋዊ ርክክብ ማካሄድ እንደሚጠበቅ አዲስ ማለዳ ከመረጃው ተመልክታለች።

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን፣ የትግራይ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ እንዲሁም በቱርኪዬ ትብብርና ድጋፍ ማስተባበሪያ ኤጀንሲ በተቋቋመው የባለሙያዎች ቡድን ስራው ቁጥጥር ይደረግበታል ተብሏል።

ፕሮጀክቱ የመስጂዱን ጥንታዊና ባህላዊ ይዘት ሳይለቅ በጥንቃቄ ለመስራት “ከፍተኛ” የቅርስ ጥበቃ መስፈርት እንደተዘጋጀ በስምምነቱ ተቀምጧል።

የአል ነጃሺ መስጂድ እድሳት ስምምነት በኢትዮጵያ እና በቱርክ መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ ግንኙነት የሚያሳይ “ጠንካራ ምልክት ሆኖ ያገለግላል” ሲሉ የሁለቱ አገራት ባለስልጣናት ገልጸዋል።

በአፍሪካ የመጀመሪያው መስጂድ እንደሆነ የሚታመነው የአል ነጃሺ መስጂድ ለዓለም ሙስሊሞች ትልቅ ዋጋ ያለው በመሆኑ የጥገና ስራው ይህ ታሪካዊ ቦታ ለትውልድ መቆየቱን ያረጋግጣል ተብሏል።

 

Source: Link to the Post

Leave a Reply