በሱዳን በኩል “የኢትዮጵያ ሚሊሻዎች” እንዲሁም በሶማሊያ የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል ድንበር ጥሰዋል ተባለ

ረቡዕ ሰኔ 19 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የሶማሊያ መንግስት የኢትዮጵያ ወታደሮች “በሕገ ወጥ” መንገድ ድንበር ተሻግረዋል በማለት በመንግስታቱ ድርጅት ፊት ወነጀለች።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሶማሊያ አምባሳደር አቡከር ዳሂር በድርጅቱ የጸጥታ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ እንደገልጹት “ባለፉት ሳምንታት የአትሚስ (የአፍሪካ ሕብረት ተልዕኮ) አባል ያልሆኑ ወታደሮች በሶማሊያ የተለያዩ የድንበር አቅጣጫዎች ገብተዋል”።

በአሁኑ ሰዓት 3 ሺህ የሚጠጉ የኢትዮጵያ ወታደሮች በአፍሪካ ሕብረት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ስር የአል ሸባብ “አሸባሪ ቡድንን” ለመታገል በሶማሊያ የሚገኙ ቢሆንም፤ እንደ አምባሳደር አቡከር ገለጻ ከነዚህ ውጭ የሆኑ ወታደሮች ድንበር ተሻግረው በመግባታቸው ከሶማሊያ የአካባቢ ጠባቂዎች ጋር ግብግብ ፈጥረዋል ተብሏል።

አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮሎኔል ጌትነት አዳነ ጋር ምላሽ ለማግኘት ብትደውልም ሳይሳካ ቀርቷል።

የሶማሊያ መንግስት ድርጊቱ የአገሪቱን ሰላም ለመበጥበጥ የሚደረግ ስለመሆኑ እያሳሰበው እንደሆነ ለጸጥታ ምክር ቤቱ የገለጹት የሶማሊያ አምባሳደር፤ የሶማሊላንድ መግባቢያ ስምምነትን ጨምሮ ሁሉም እንቅስቃሴ በዓለም አቀፍ ሕግ እና በጥሩ የጉርብትና ስሜት እንዲሆን ለኢትዮጵያ መንግስት ጥሪ አቅርበዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሱዳን መገናኛ ብዙኀን የኢትዮጵያ ታጣቂዎች ከዚህ ቀደም የይገባኛል ግጭት በተከሰተበት አል ፋሻቃ ግዛት በኩል መግባታቸውን እየዘገቡ ይገኛሉ።

በዚህ የድንበር ስፍራ “የኢትዮጵያ ታጣቂዎች” ተብለው የተገለጹት አካላት 15 ኪሎ ሜትር ወደ ሱዳን ድንበር ተሻግረው በመግባት ጥቃት እና ዝርፊያ እንደፈጸሙ ተመላክቷል። የታጣቂዎቹ ማንነት በዘገባዎቹ አልተገለጹም።

Source: Link to the Post

Leave a Reply