በሱዳን የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የሚገጥሟቸው ችግሮች …

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 7፣ 2014 በሱዳን የመኖሪያ እና ሥራ ፈቃድ ክፍያዎች ከኢትዮጵያዊያን የመክፈል አቅም በላይ በመሆቸው በርካቶች ሕጋዊ ሆኖ ለመኖር መቸገራቸው ተገለጸ፡፡ በሱዳን ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር የሆኑት ይበልጣል አዕምሮ ችግሩን ለመቅረፍ በሱዳን በኩል ልዩ ድጋፍ እና ትብብር እንዲደረግ ጠይቀዋል። አምባሳደር ይበልጣል ጥያቄውን ያቀረቡት ከሱዳን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ተጠባባቂ ሚኒስትር ጋር በችግሩ ዙሪያ በተወያዩበት ወቅት ነው፡፡

በውይይቱም ሱዳንን እንደ አገራቸው በመቁጠር በርካታ ኢትዮጵያዊያን ሱዳን ውስጥ እንደሚኖሩ በመግለጽ የሱዳን መንግስት እና ሕዝብ ለሚያሳየው መልካም አያያዝ አምባሳደሩ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ሆኖም የሱዳን መንግስት በስራ ላይ ያዋለው የመኖሪያ እና የሥራ ፈቃድ ክፍያ የኢትዮጵያዊያኑን የመክፈል አቅም በእጅጉ የሚፈታተን በመሆኑ እንዲሻሻልና ድጋፍ እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡

በዚህም ወደ ሀገራቸው በተሽከርካሪ መመለስ ለሚፈልጉ ኢትዮጵያዊያን አዲሱ የመውጫ ቪዛ ክፍያ እንዲነሳና ቀደም ሲል በነበረው ክፍያ መውጣት እንዲችሉ፣ የመኖሪያ ፈቃድ በማውጣት ሕጋዊ ሆነው መኖር ለሚሹት ደግሞ ለቅጣት የሚጠየቀው ክፍያ እንዲነሳላቸው ነው የተጠየቀው፡፡ የሱዳን የሀገር ውስጥ ተጠባበቂ ሚኒስትሩ ሌተናል ጄኔራል አናን ሃሚድ ሞሃመድ በበኩላቸው ኢትዮጵያዊያን የሚገጥሟቸውን ችግሮች እንደሚረዱ ገልፀው በችግሮቹ ዙሪያ የተነሳውን ጥያቄ
ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመመካከር ለመፍታት ጥረት እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል። ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን በጋራ መዋጋት እና በሁለቱ አገሮች መካከል ያሉ የትብብር መድረኮችን እንደገና ማንቀሳቀስ እንደሚገባም ሚኒስትሩ መናገራቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply