አርብ ሰኔ 30 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ)
በኢትዮጵያ የስርቆት ወንጀል በብዛት ሲፈጸም የሚስተዋለው በወንዶች ቢሆንም፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በወንጀሉ ተሳታፊ የሚሆኑ ሴቶች እየተበራከቱ መምጣታቸውን የአዲሰ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ለአዲስ ማለዳ ጠቁሟል።
የአዲሰ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ፤ “ከባህላችን አንጻር ማህበረሰቡ ለሴት ልጅ ትልቅ ክብር ስላለውና ሴቶች በስርቆት ወንጀል ይሰማራሉ ብሎ ብዙም ስለማያስብ፣ ለወንጀል ድርጉቱ ተጋላጭ እየሆኑ ነው።” ብለዋል፡፡
“በተለይ ሴቷ መልከ መልካም ከሆነች፤ ሰዎች በቀላሉ የመቀራረብ ባሕሪ ያሳያሉ፣ ወሬ ይጀምራሉ፣ ወንጀል ፈጻሚዋም ወደምትፈልገው አቅጣጫ በማስገባት ዘረፋ ትፈጽማለች።” ነው ያሉት።
በስርቆት ወንጀል የሚሳተፉ ሴቶች ቆንጆ ሆነው ወንዶችን ሲቀርቧቸው “ወዳኝ ነው የቀረበችኝ” ከማለት ባለፈ ወንጀል ለመፈጸም ነው ብለው ስለማይገምቱ፤ የወንጀሉ ፈጻሚ ሴቶች ወንዶችን ወደሚፈለጉበት ቦታ ወስደው ይዘረፏቸዋልም ሲሉ አክለዋል፡፡
“በአንድ ተሽከርሪ ውስጥ 10 ሴቶች እና ኹለት ወንዶች ቢኖሩ እንኳን ወንዶቹን እንጅ ሴቶቹ ይሰርቃሉ ብሎ የሚጠረጥር አካል የለም።” ያሉት ዳይሬክተሩ፤ በዚህም በርካታ ሰዎች ለስርቆት ወንጀል ተጋላጭ እየሆኑ ነው ብለዋል፡፡
ስለሆነም ከቀን ወደ ቀን የስርቆት ወንጀል መልኩን እየቀያየረ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ በስርቆት ወንጀል የሚሳተፉ ሴቶች ቁጥርም እየጨመረ መምጣቱ ነው የተገለጸው።
በስርቆት ወንጀል የተሰማሩ በርካታ ወንዶችም ሴቶችም በየወቅቱ በቁጥጥር ሥር እየዋሉ መሆኑን የጠቀሰው ፖሊስ ኮሚሽኑ፤ በተለይ “ሿሿ” በሚባል የስርቆት ስልት በርካቶች እየተጭበረበሩ መሆኑን አመላክቷል።
የስርቆት ወንጀል በትራንስፖርት ላይ በብዛት እንደሚፈጸም በመግለጽም፤ ሕብረተሰቡ ከማያውቀው ሰው ጋር ሰለራሱ ሚስጥር ከማወራትና የተለየ ግንኙነት ከመፍጠር እንዲቆጠብ፣ ብሎም ከጊዜው ጋር አብሮ መፍጠን እንዳለበት ጠቁሟል።
Source: Link to the Post