በስልጤ ዞን የበልግ ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ ከ130 በላይ አባወራዎች ተፈናቀሉ

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል፣ ስልጤ ዞን፣ ስልጢ ወረዳ የበልግ ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ ከ130 በላይ አባወራዎች ከመኖሪያ ቤታቸው መፈናቀላቸው ተነግሯል። ለበልግና ለመኸር የተዘጋጀ የእርሻ መሬት በጎርፍ እንደተያዘም ተገልጿል።
የዞኑ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ወሲላ አሰፋ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፣ ከመደበኛው መጠን በላይ እየጣለ በሚገኘው የበልግ ዝናብ ሳቢያ ጎፍለላ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑ 132 አባወራዎች ከመኖሪያ ቤታቸው ተፈናቅለዋል።
150 ቤቶች እና 235 ሄክታር የእርሻ መሬት በጎርፍ እንደተያዙም የጠቆሙት ሃላፊዋ፤ አደጋው በሰዎች ሕይወትና ንብረት ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ጥረት መደረጉን አመልክተዋል።
“በአሁኑ ሰዓት ከመኖሪያ ቤታቸው የተፈናቀሉ አባወራዎች በጊዜያዊ መጠለያ እንዲጠለሉ አድርገናል” ያሉት ሃላፊዋ፣ ከፌደራልና ክልል ተቋማት ጋር በመቀናጀት ለእነዚሁ ተፈናቃዮች የምግብ ዕርዳታ እየተሰጠ መሆኑን ገልፀዋል።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል፣ ሃላባ ዞን በደረሰው የጎርፍ አደጋ የአምስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን የዞኑ አስተዳደር ማስታወቁ የሚታወስ ነው። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ)፣ አንድ ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ መሆናቸውን በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት አመልክቷል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply