በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ ጥር 14 ቀን 2015ዓ.ም. በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀ…

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

ጥር 14 ቀን 2015ዓ.ም. በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሐሮ ባለወልድ ቤተ ክርስቲያን የተፈጸመውን ሕገወጥ የኤጲስ ቆጶሳት ሹመትን ተከትሎ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ጥር 18 ቀን 2015ዓ.ም. ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ የተከናወነው ድርጊት የቤተ ክርስቲያኒቱን ዶግማ፣ ቀኖና አስተዳደራዊ መዋቅር የጣሰ ሕገወጥ አድራጎት መሆኑን አጽንኦት ሰጥቶ በመወያየት ሕገወጡን ሹመት ያከናወኑትና ተሿሚዎችን በቤተ ክርስቲያናችን ቀኖናዊ ሥርዓት ከዲቁና ጀምሮ የነበራቸውን ማዕረገ ክህነት በሙሉ በመሻር ከቤተ ክርስቲያኒቱ አባልነት አውግዞ መለየቱ የሚታወስ ነው፡፡

ምንም እንኳን የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በውሳኔው ውግዘቱ እንደተጠበቀ ሆኖ በድርጊታቸው ተጸጽተው እና ከስህተታቸው ተመልሰው በቤተ ክርስቲያኒቱ ሥርዓት መሠረት የሚሰጣቸውን ቀኖና ተቀብሎ ለመመለስ ዝግጁ ከሆኑ የቤተ ክርስቲያኒቱ የይቅርታ በር ክፍት መሆኑን በማሳወቅ መግለጫ የሰጠ ቢሆንም ግለሰቦቹ ከስህተታቸው ተምረው በይቅርታ እድሉ ከመጠቀም ይልቅ በሕገወጥ መንገዱ ቀጥለውና ውግዘቱን ጥሰው በቤተ ክርስቲያኒቱ ሕጋዊ መዋቅራዊ አደረጃጀት መሠረት ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በቅዱስ ሲኖዶስ ተመድበው በሚያገለግሉባቸው አህጉረ ስብከት ላይ እርስ በርሳቸው በመመዳደብ እያደረጉት የነበረውን ሕገወጥ እንቅስቃሴ መንግስት በሕግ የተጠላበትን ሕግን የማስከበር ኃላፊነት በመወጣት የቤተ ክርስቲያናችንን ተቋማዊ ልዕልና እንዲያስከብርልን ከመግለጫም አልፎ በደብዳቤ ያቀረብነው ጥያቄ ተቀባይነት አጥቶ በሕገወጥ መንገድ የተሾሙት ግለሰቦች በመንግሥታዊ የፀጥታ አካላት ታጅበው በኦሮምያ ክልል የሚገኙትን አህጉረ ስብከት፣ ወረዳ ቤተ ክህነት፣ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትን በኃይል ሰብረው ተቋማቱን በመውረር ሀብትና ንብረት የተዘረፈ ሲሆን ይህም ሕገወጥ ድርጊት በሚከናወንበት ወቅት ሕገ ቤተ ክርስቲያናችን አይጣስም፣ ሲኖዶሳችን አይከፈልም፣ ቀኖናችን አይደፈርም በማለት በጽናትና በአንድነት ድርጊቱን የተቃወሙት ምዕመናን፣ ወጣቶችና አገልጋይ ካህናት እንዲሁም በየደረጃው ያሉ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልዩ ልዩ የሥራ ኃፊዎች በተለይም የሻሸመኔና አካባቢው ምእመናንና አገልጋይ ካህናት ለሞት፣ ለአካልና የሞራል ጉዳት፣ ለእስራትና እንግልት ተዳርገዋል፡፡

በዚህም ምክንያት ቅዱስ ሲኖዶስ ችግሩን እና ፈተናውን የማሳለፍ ሥልጣን ሁሉ ባለቤት የሆነው እግዚአብሔር አምላካችን በምሕረት አይኑ ተመልክቶ የመጣውን ፈተና ያስወግድልን ዘንድ በጾመ ነነዌ ለ3 ቀናት ሁሉም የቤተ ክርስቲያኒቱ እምነት ተከታዮች ማቅ ለብሰው በጸሎትና በምህላ ወደ እግዚአብሔር እንዲያመለክቱ በወሰነው መሠረት በቤተ ክርስቲያናችን ታሪክ ተፈጽሞ በማያውቅ ሁኔታ እንኳንስ ልጆቿ ምእመናን ይቅርና እራሷ እናት ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም የሀዘን መገለጫ የሆነውን ጥቁር ማቅ ለብሳ ከሀገር አቀፍም አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሀዘኗን ገልጣለች፡፡
የእናት ቤተ ክርስቲያንና የልጆቿ ምዕመናን እንባና ጸሎት በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት በማግኘቱ ለውይይት ዝግ የነበረው የመንግስታችን በር ለውይይት ተከፍቷል፡፡ የደረሠብን የጉዳት ከፍተኛነት በሀገራችን መንግስታዊ ሚዲያዎች ዘንድ ቦታ ቢያጣም አለም አቀፍ ሚዲያዎችና የቤተ ክርስቲያናችን የሚዲያ ተቋማት ለአለም አቀፍ ማህበረሰብ እንዲደርስ በማድረጋቸው ችግሩን ከእኛም አልፎ በሁሉም አኃት አብያተ ክርስቲያናት፣ የአለም አብያተ ክርስቲያናት ሕብረት፣ የምሥራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት እና ሌሎች ሲቢክ ማህበራት ድርጊቱን በማውገዝ ለእናት ቤተ ክርስቲያናችን ያላቸውን አጋርነት ገልጸዋል፡፡ በዚህም በችግራችን ወቅት ከጎናችን ለቆሙት አካላት በሙሉ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አሁንም በድጋሚ ከፍ ያለ ምስጋናዋን ታቀርባለች፡፡

በመጠቀልም ክቡር የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ባመቻቹት የውይይት መድረክ በተወከሉ ብፁዓን አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች በኩል በተደረገው መጠነ ሰፊ ውይይት መሠረት ባለ10 ነጥቦች ላይ የጋራ ስምምነት በተደረሰው መሠረት ሦስቱ የቀድሞ አባቶች የካቲት 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ወደ ጽርሐ መንበረ ፓትርያርክ መጥተው በቀድሞ በዓታቸው ተወስነው እስካሁን የቆዩ ሲሆን 20ዎቹ ተሿሟዎች ደግሞ በስምምነቱ መሠረት ለውሳኔው ተገዥ መሆናቸውን በመግለጽ መጋቢት 15 ቀን 2015 ዓ.ም. እያንዳንዳቸው በጽሑፍ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ባቀረቡት መሠረት ውግዘቱ እንዴት ሊፈታ እንደሚገባ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንት ጉባኤ የውሳኔ ሐሳብ እንዲያቀርብ በታዘዘው መሠረት የቤተ ክርስቲያኒቱን የቀኖና ቅዱሳት መጻሕፍት ዋቢ በማድረግ የውሳኔ ሐሳቡን ያቀረበ ሲሆን እንደሚከተለው በአጭሩ ተገልጿል፡፡

ሀ. “ኢይክል ሰብእ ነሢአ ፀጋ ለሊሁ ወኢምንተኒ እመ ኢተውህበ ሎቱ እምሰማይ” ሰው ከእግዚአብሔር ካልተሰጠው በስተቀር እርሱ ራሱ ጸጋን ገንዘብ ማድረግ አይችልም” (ዮሐ. 3፣27) በማለት በቅዱስ ወንጌል እንደተነገረው የእግዚአብሔር ጸጋ ከላይ የሚሰጠው በቅንነት፣ በትሕትና፣ በትዕግሥትና በጸሎት በመሳሰለው እንጅ በሥርዓተ አልበኝነትና በሕገወጥ የድፍረት መንገድ የሚገኝ የእግዚአብሔር ጸጋ የለም፤ አልኖርም፤ አልነበረም፤ ወደፊትም አይኖርም፡፡

ለ. ብርሃና ለቤተ ክርስቲያን የተባለው ደጉ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስም “ወአልቦ ዘይነሥእ ክብረ ለርእሱ ዘእንበለ ዘጸውዖ እግዚአብሔር በከመ አሮን” እንደ አሮን በእግዚአብሔር ከተጠራ በቀር ማንም ክብርን ለራሱ የሚወስድ የለም ሲል ክብረ ክህነትን በሚገባ ገልጿል፡፡ (ዕብ.5፡4) እንዲህም በመሆኑ በአሁኑ ሰዓት ከቅዱስ ሲኖዶሱ ውሳኔ ውጭና ቅዱስ ፓትርያርኩ በሌሉበት በድብቅ የተፈጸመው ሕገወጥ ሢመተ ክህነት ለሿሚውም ሆነ ለተሿሚው የእግዚአብሔርን ጸጋ በራስ ፈቃድ እንደመውሰድ ስለሚቆጠር ከፍተኛ የሆነ የዶግማ ጥሰት ተግባር ነው፡፡

ሐ. ከቅዱስ ቃሉ እንደተማርነው “ቀዳሚሃ ለጥበብ ፈሪሀ እግዚአብሔር – የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው” (መዝ.109፣10 ምሳ.1፣7) ይህንም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃል መሠረት በማድረግ ስግዱ ለእግዚአብሔር በፍርሀት – ለእግዚአብሔር በፍርሀት ስገዱ (መዝ.28፣2)

ተቀነዩ ለእግዚአብሔር በፍርሀት – ለእግዚአብሔር በፍርሀት ተገዙ (መዝ.2፣11)

ንትነሣእ በፍርሀተ እግዚአብሔር – እግዚአብሔርን በመፍራት እንነሣ (ቅዳ.ማ) በማለት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እስከ እስትንፋሰ ደኃሪት መልእክቷን ዘወትር ታስተላልፋለች፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት ይህ ሆኖ እያለ አሁን የተፈጸመው ድርጊት ግን በከፍተኛ ድፍረትና በሕገወጥ መንገድ ከመፈጸሙና የሥልጣነ ክህነትን ክብር ከማጉደፉም በላይ ከውግዘትም በኋላ ከጥፋቱ ባለመማር ሕገወጥነትን እንደ ሕጋዊነት፣ ጥፋትን እንደ ልማት፣ ሐሰትን እንደ እውነት፣ የነፍስ ጥፋትን እንደ ነፍስ ማዳን ተቆጥሮ በልበሙሉነት የአህጉረ ስብከትና የአጥቢያ አበያተ ክርስቲያናት በር በኃይል ተሰብሮ የመውረር ሕገወጥ ተግባር ተፈጽሟል፡፡ ይህም ድርጊት ከውግዘት በኋላ በመሆኑ ሕገ እግዚአብሔርን እያወቁ ወደጎን በመተው የተፈጸመ ድርጊት በመሆኑ የዶግማ ጥሰት ነው፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply