በስንዴ እጥረት ምክንያት የዱቄት ፋብሪካዎች ስራ እያቆሙ ነው ተባለ፡፡መንግስት በስንዴ ምርት ላይ ከፍተኛ ለውጥ አምጥቼ ለኤክስፖርት ደርሻለሁ ቢልም የሃገር ውስጥ ፋብሪካዎች ግን በምርት አጥ…

በስንዴ እጥረት ምክንያት የዱቄት ፋብሪካዎች ስራ እያቆሙ ነው ተባለ፡፡

መንግስት በስንዴ ምርት ላይ ከፍተኛ ለውጥ አምጥቼ ለኤክስፖርት ደርሻለሁ ቢልም የሃገር ውስጥ ፋብሪካዎች ግን በምርት አጥረት እየተቸገሩ እንደሚገኙ እየገለጹ ነው፡፡
በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የስንዴ ምርት በብዛት እንዲመረት ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ሲሆን ለኤክስፖርት የሚሆን ስንዴ እንዲያዘጋጁም ክልሎች ኮታ እንደተጣለባቸው ሲነገር ነበር፡፡

በቅርቡም ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በተገኙበት ከኦሮሚያ ክልል የስንዴ ምርትን ወደ ውጭ መላክ መጀመሩ አይዘነጋም፡፡
ይህ በሆነ ማግስት ግን የዱቄት፣ፓስታና መኮሮኒ አምራች ፋብሪካዎች የስንዴ ምርት እጥረት ገጥሞናል፤በዚህም ስራ ለማቆም ተገደናል ብለዋል፡፡

የዱቄትና የዱቄት ውጤቶች አምራቾች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ሙሉነህ ለማ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንደተናገሩት፤ ስንዴ በአሁኑ ወቅት ኮንትሮባንድ ሆኗል፤ማንም እንደፈለገ መግዛትም ሆነ መሸጥ አይችልም ብለዋል፡፡

መንግስት ለኤክስፖርት የሚሆን ስንዴን ለማግኘት ሲል ዩኒዮኖች ብቻ እንዲገዙ ፈቀደ፣ለዱቄት አምራቾችም በዩኒዮኖች በኩል ታገኛላችሁ ተባሉ፣በኋላም 12 ባለሃብቶች ተመርጠው ወደ ስራ ገቡ፣ዱቄት አምራቾች ግን ስንዴ ሊያገኙ አልቻሉም ብለዋል፡፡

ይህ ችግር ከተፈጠረ 2 ወራትን አስቆጥሯል የሚሉት አቶ ሙሉነህ፣አምራቾች በእጃቸው ያለችውን ስንዴ እየቆጠቡ ሲጠቀሙ ቆይተው አሁን ላይ ስራ ማቆም ደረጃ ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል፡፡በዚህም በዳቦ ላይ የሚስተዋለው ጭማሬ እንዳለ ሆኖ የ1 ኪሎ መኮሮኒ ዋጋ ከ40 ብር ወደ 80 ብር ከፍ እንዲል አድርጎታል ነው የተባለው፡፡

እንደ አቶ ሙሉነህ ገለጻ በአሁኑ ወቅት ስንዴ እንደ ኮንትሮባንድ ተቆጥሮ በየኬላዎች በፍተሻ እየተያዘ ነው፡፡ በዚህም አምራቾች ገዝተው መተቀም አይችሉም፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች መጋዘን ላይ ስንዴ የተገኘባቸው ዱቄት ፋብሪካዎችም ሆነ ነጋዴዎች በህገ ወጥ መንገድ ግብይት ፈጽማችኋል በሚል ወከባ እየደረሰባቸው እንደሚገኝም አንስተዋል፡፡

በመሆኑም ከሁሉም ነፊት የሃገር ውስጥ ፍላጎትን ማሟላት ይቀድማልና ችግሩን ለመፍታት መንግስት ትኩረት እንዲሰጥ አቶ ሙሉነህ ጠይቀዋል፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን

የካቲት 14 ቀን 2015 ዓ.ም

ለተጨማሪ መረሃዎች የቴሌግራምና የዩቲዩብ ቻናሎቻችንን ይቀላቀሉ!

Telegram https://t.me/ethiofm107dot8
YouTube https://www.youtube.com/@onelovebroadcast

ያሎትን አስተያየት እና ጥያቄ በአጭር መልዕክት 6321 ላይ ይላኩልን።
ከኛ ጋር ስለሆናችሁ ከልብ እናመሰግናለን።

Source: Link to the Post

Leave a Reply