You are currently viewing በሸዋ አጣዬ እና ሸዋሮቢት አካባቢ የህዝብን ሰላም ለማስከበር በስምሪት ላይ በነበሩ የጸጥታ ኃይሎች እና በህዝብ ላይ የተቀናጀ ተደጋጋሚ ጥቃት በመክፈት ጉዳት ባደረሱ አጥፊዎች ላይ የእርምት…

በሸዋ አጣዬ እና ሸዋሮቢት አካባቢ የህዝብን ሰላም ለማስከበር በስምሪት ላይ በነበሩ የጸጥታ ኃይሎች እና በህዝብ ላይ የተቀናጀ ተደጋጋሚ ጥቃት በመክፈት ጉዳት ባደረሱ አጥፊዎች ላይ የእርምት…

በሸዋ አጣዬ እና ሸዋሮቢት አካባቢ የህዝብን ሰላም ለማስከበር በስምሪት ላይ በነበሩ የጸጥታ ኃይሎች እና በህዝብ ላይ የተቀናጀ ተደጋጋሚ ጥቃት በመክፈት ጉዳት ባደረሱ አጥፊዎች ላይ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ ተጠየቀ፤ ለተፈናቀሉ ዜጎችም አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደርሳቸው ጥሪ ቀርቧል። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ጥር 19 ቀን 2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ሸዋ ሸዋ ሰላም እና ልማት (ሸዋሰማ)፣ መንዝ እና ግሼ ልማት ማህበር (ወግልማ)፣ ሸዋ የአማራ ወጣቶች ማህበር፣ይፋት ልማት ማህበር (ይልማ) እና ማህደረ ሸዋ በጎ አድራጎት ማህበር በወቅታዊ ጉዳይ በጋራ ባወጡት መግለጫ በአጣዬ፣ በሸዋሮቢት እና አካባቢው እየተፈፀመ ያለው ተደጋጋሚ ጥቃት መፍትሄ እንዲበጅለት ጠይቀዋል። በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አካባቢዎች በሰላማዊ ዜጎች እና የህዝብን ሰላም ለማስከበር በስምሪት ላይ በነበሩ የጸጥታ ኃይሎች ላይ የተከፈተው የተቀናጀ ተደጋጋሚ ጥቃት ዘላቂ መፍትሄ እንዲሰጠው እና ተመጣጣኝ የእርምት እርምጃ በአጥፊዎች ላይ እንዲወሰድ እንዲሁም ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ እንዲደርስ ተጠይቋል። በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን እና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ልዩ ዞን አጎራባች ወረዳዎች እና ቀበሌዎች በተለይም በኤፍራታና ግድም ወረዳ፣ በወቀት ወረዳ፣ በአንጾኪያና ገምዛ ወረዳ በአጣዬ ከተማ አስተዳደር፣ በካራቆሬ፣ በቆሪሜዳ ፣ በማጀቴ ፣ በየለን፣ በተሬ ፣ በጀውሀ፣ በአርሶ አምባ-ዘንቦ ፣ በመንተኬ-ሸረፋ ወ.ዘ.ተ ቀበሌዎች የኦነግ-ሸኔ ኃይል የተለያዩ የፀረ-ሰላም ሃይሎችን በማስተባበር እና ከአማራ ጠል ኃይሎች ከፍተኛ የስንቅ እና የትጥቅ ድጋፍ በማግኝት በማያቋርጥ ሁኔታ ባለፉት አራት የመከራ አመታት በንጹሃን ዜጎቻችን ላይ ከፍተኛ ጥቃት ተፈጽሟል፡፡ ንጹሃን አማራዎች በማንነታቸው ብቻ ተለይተው በግፍ ተገድለዋል። ቤት ንብረታቸው ወድሟል፣ ተዘርፏል፡፡ ይህ ሁሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እና ወንጀሎች በተደጋጋሚ ቢፈጸሙም በወንጀል ድርጊቶቹ የተሳተፉ አካላት እና ከጀርባ ያሉት የሴራ ፖለቲካ ሃይሎች በህግ አግባብ አልተጠየቁም። ወንጀለኞች በህግ ባይጠየቁም በግፍ ቤተሰቦቻቸውን ያጡትን በማጽናናትና እንዲሁም ቤት ንብረታቸው የወደመባቸውንና የተፈናቀሉትን መልሶ በማቋቋም ወደ ቦታቸው ተመልሰው እንዲያገግሙ እየተደረገ ባለበት በአሁኑ ወቅት ሆን ተብሎ በተደራጀ ኃይል ጭካኔ በተሞላበት ደባ ንጹሃን በግፍ እንዲገደሉና ድጋሚ ከተሞች እንዲወድሙ እየተደረገ ነው። በአካባቢው እጅግ በሚያሳስብ እና በሚያሳፍር ደረጃ፣ በጸጥታ ኃይሎቻችን በተለይም በአማራ ልዩ ኃይል፣ በፌደራል ፖሊስ፣ በሀገር መከላከያ ሠራዊት እንዲሁም በአማራ ሚሊሻ ላይ በቡድን መሳሪያ እና ሎጂስቲክ ጭምር በታገዘና በተቀናጀ መልኩ ጥቃት ሲፈጸም ማየት እየተለመደ መጥቷል። ይህም ሃገርን የማፍረስ እና ዜጎችን ሰላም የመንሳት አንዱ የጥፋት መንገድ መሆኑን መላው ኢትዮጵያውያን ሰላም ወዳዶች ሁሉ ሊገነዘቡት እና ለዘላቂ መፍትሄው የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሊያደርጉበት የሚገባ አሳሳቢ ችግር ነው። የሽብርተኛው የኦነግ-ሸኔ የጥፋት ኃይል አጋሮቹ በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ልዩ ዞን በአርጡማ ፉርሲ ወረዳ እና በጅሌ ጥሙጋ ወረዳ ውስጥ በሚገኙ ቀበሌዎች በተለይም በጋንጋሀና በደዌ-ሃረዋ ስልጠና ሲወስድ የአማራ ክልል የማያዳግም እርምጃ አለመውሰዱ እንዲሁም ከዚህ በፊት በህዝባችን እና በልዩ ሃይሎቻችን ላይ ግፍ የፈጸሙ ኃይሎች ለህግ አለማቅረቡ ህዝባችንን ለተደጋጋሚ ጥቃት እንዲጋለጥ አድርጎታል፡፡ በተለይም የሰሜን ሸዋ ዞንን ጨምሮ በየደረጃው የሚገኘው አስተዳደር ያለውን እምቅ አቅም በመጠቀም እና ህዝቡን በማስተባበር በተደጋጋሚ የሚፈጸመውን ጥቃት መከላከል አለመቻሉ ህዝባችን ለተደጋጋሚ ከፍተኛ ሞት፣ ስደት፣ መፈናቀል፣ ውድመትና አለመረጋጋት ሰለባ እንዲሆን አድረጎታል፡፡ ተደጋጋሚ ጥቃት የሚፈጽመው አሸባሪውና ጸረ-ሰላም ቡድን ከፍተኛ ዝግጅት አድርጎ በቡድን መሳሪያ በታገዘ ጥቃት ጥር 13/2015 ዓ.ም ጀውሀ ቀበሌ የሚገኘውን የአማራ ልዩ ኃይል ድንገት በመውረር በርካታ የልዩ ኃይል አባላትን፣ የፌደራል ፖሊስና ንጹሃን ዜጎችን በግፍ ከገደለ በኋላ ጥቃቱን በማስፋት በድጋሚ በጀውሀ እና በሰንበቴ የነበረውን የአማራ ልዩ ኃይል ጥር 15/2015 ዓ.ም የተሳሳተ ግምትን ይዘው የሚጓዙ የተለያዩ የጥፋት ቡድኖችን በማስተባበር ከበባ በማድረግ በግፍ ጥቃት ፈጽመውበታል። አሸባሪውና ጸረ-ሰላም ቡድኑ ምንም የጦር መሳሪያ ባልታጠቁ ንጹሃን ዜጎች ላይ እያደረሰ ያለውን መጠነ ሰፊ ጥቃት ለማስቆም በተሰማሩ የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የፌደራል ፖሊስ አባላት ላይም ጉዳት አድርሷል፡፡ በጥቃቱ የተገደሉ ንጹሃን ዜጎች ቁጥርም ከፍተኛ ነው፡፡ ይህ የጥፋት ኃይል በኤፍራታና ግድም ወረዳ እና በቀወት ወረዳ ልዩ ልዩ አካባቢዎች ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽሟል፣ ሃብት ንብረት አውድሟል፣ ዘርፏል፡፡ የጥፋት ኃይሉ ከብሔረሰብ አስተዳደሩ አንዳንድ አመራሮች፣ ባለሃብቶች እና የኃይማኖት አባቶች ጭምር በሚያገኘው ከፍተኛ ድጋፍ ጥቃቱን ኃይማኖታዊ እና የብሔር መልክ እንዲይዝ ባደረገው እኩይ ጥረት በመተሳሰብ እና አብሮ በኖረው ማህበረሰብ መካካል መቃቃርና አለመተማመን በመፍጠር ለዘመናት የተገነባውን አብሮነት በመናድ በአካባቢው በሚገኝው የአማራ ህዝብ ላይ የማያቋርጥ ጭፍጨፋ እየፈጸሙ እና እያስፈጸሙ ይገኛሉ፡፡ አንዳንድ ሃላፊነት የጎደላቸው የፖለቲካ ሃይሎችም ይህን አጋጣሚ ለእኩይ ተግባራቸው ሲጠቀሙበት ጭምር ይታያል፡፡ ይህ አደገኛ ሀገር አፍራሽ ተግባር እንደሆነ ሁሉም ሊገነዘበው ይገባል፡፡ ስለሆነም፡- 1. የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በዚህ የጥፋት ኃይል ላይ የማያዳግም እርምጃ በመውሰድ የአካባቢውን ሰላም በማረጋገጥ፣ ህጋዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ እንጠይቃለን። 2. የሰሜን ሸዋ ዞን መስተዳደር እና በየደረጃው ያሉ አመራሮች የህዝብን ደህንነት የማስጠበቅ ተቀዳሚ ተልዕኳቸውን እንዲወጡ እንጠይቃለን። 3. የፍትህ አካላት እና የሰብአዊ መብት ድርጅቶች እየደረሰ ያለውን ጉዳት በሚገባው ልክ በመገንዘብ አስፈላጊውን ማስረጃ በማሰባሰብ በህግ መጠየቅ ያለባቸው አካላትን ሁሉ በመጠየቅ ፍትህ ይረጋገጥ ዘንድ ለችግሩ ትኩረት ሰጥታችሁ እንድትንቀሳቀሱእንጠይቃለን። 4. የሚዲያ አካላት ችግሩን በአግባቡ ዘግቦ ለዘላቂ መፍትሄው ግብአትን በማመንጨት መስራት እንጂ በሰብአዊነት እና በፍትህ ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት ለማድበስበስና ለመሸፋፈን መሞከር ተገቢ እንዳልሆ እየገለጽን አጠቃላይ የችግሩን መንስዔ፣ ሂደት እና እየደረሰ ያለውን ጉዳት በአግባቡ በመዘገብ ለህዝብና ሃገር ተገቢውን መረጃ በወቅቱ ታደርሱ ዘንድ እንጠይቃለን። 5. የግብረሰናይ ድርጅቶች በጥቃቱ ለተፈናቀለው ከ250,000 በላይ ህዝብ አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያገኝ በሚቻለው አቅም ሁሉ እንድትንቀሳቀሱ እና በዘላቂነት ለማቋቋም በሚደረገው ጥረትም ተሳትፎ እንድታደርጉ እንጠይቃለን፡፡ ክብርና ሞገስ የንጹሃንን ደህንነት ለማስጠበቅ ዋጋ እየከፈሉ ላሉ ጀግኖች ሰማዕታት!!!

Source: Link to the Post

Leave a Reply