
በሸዋ የደራ ወረዳ መስተዳድር ለአማራ ገበሬዎች የአፈር ማዳበሪያ እንዳይሰጥ አገደ፤ በሲኖ ተጭኖ ወደ ቱቲ የአማራ ቀበሌዎች ሲጓጓዝ የነበረ ማዳበሪያም እንዲመለስ ማድረጉ ተገልጧል። አማራ ሚዲያ ማዕከል (አሚማ) ሰኔ 28/2015 ዓ/ም_ አዲስ አበባ ኢትዮጵያ የኦሮሚያ ብልፅግና ዘረኛ አካሄድ አሁን ግን አይን ያወጣ እና በጋሃድ እየታዬ ይገኛል የሚሉት ምንጮች በሸዋ ደራ ወረዳ ውስጥ የሚኖሩ አማራዎች ላይ በተለያዩ ጊዜያት የአገዛዙ ሌላኛው ጸረ አማራ ክንፍ አሸባሪው ኦነግ ሸኔ ከሚፈጽመው ጥቃት በተጨማሪ አቶ ሽመልስ አብዲሳ የሚመራው የኦህዴድ ብልጽግና ክልላዊ አገዛዝ ግፍ ፈጽሟል፤ እየፈጸመም ይገኛል ሲሉ ገልጸዋል። ከዚህም በተጨማሪ ከጥቃት እና ከመሳደድ ለተረፉ ለደራ አማራዎች የአፈር ማዳበሪያ እንዳይደርሳቸው መመሪያ አስተላልፏል ሲሉ ነው የአሚማ ምንጮች የገለጹት። ለዚህ እንደማሳያ የጠቀሱትም ሰኔ 28/2015 የአፈር ማዳበሪያ ጭኖ ወደ ቱቲ ሰኞ ገበያ እየሄደ የነበረ ሲኖ ካሶኒ መኪናን ካቢ ጎለልቻ በተባለ ቀበሌ ከመድረሱ በኦህዴድ ብልጽግና የጸጥታ ኃይሎች እንዲመለስ ስለመደረጉ ገልጸዋል። በደራ ያለ አማራን በጠላትነት ከሚያዩ አመራሮች መካከል የወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤት አመራሮች እና ሌሎች ጽንፈኛ የወረዳ አመራሮች ዋነኛ የአድሎ ሴራ ጠንሳሽ ስለመሆናቸው ጠቁመዋል። በሸዋ ደራ የሚገኙ እስር ቤቶች የሀይማኖት አባቶች፣ ወጣቶች ፣ሴቶች እና ህጻናት በአሸባሪ ኦነጋዊያንን እንዳይጨፈጨፉ፣ ጉንዶ መስቀልን ጨምሮ በደራ ያሉ ከተሞች፣ በውስጣቸው ያሉ ባንኮችን ጨምሮ የመንግስትና የግል ተቋማት እንዳይዘረፉ ከፍተኛ ተጋድሎ ባደረጉ የህዝብ ባለውለታዎች ተሞልተው ይገኛሉ። ለዚህ እንደ ማሳያ ፊቼ ላይ በአማራዊ ማንነታቸው ብቻ ያለፍትህ ታጉረው እየተሰቃዩ የሚገኙት እነ መቶ አለቃ ኢንጅነር ሀብታሙ ድፍሩ ተጠቃሽ ስለመሆናቸው ተመላክቷል። በመጨረሻም ከአሁን ቀደም በተደጋጋሚ የተፈጸመውን እና እየተፈጸመ ያለውን አማራን በሁለንተናዊ መልኩ በተለይም በሰው ኃይል እና በኢኮኖሚ በማዳከም ወደ ድህነት አረንቋ የመውሰድ የኦህዴዳዊያንን ሴራ በማጋለጥ እና በመታገል ረገድ የሚዲያ ተቋማት እና ዘረኝነትን የሚጠየፉ እና የደራ አማራ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች ሁሉ ከጎናቸው እንዲሆኑ የተማጽኖ ጥሪ ቀርቧል።
Source: Link to the Post