በሸገር ከተማ አስተዳደር የነዋሪዎች መታወቂያ ካርድ እስከ አራት ሺሕ ብር እየተሸጠ መሆኑ ተሰማ

በቅርቡ በአዲስ አበባ ዙሪያ በተዋቀረው ሸገር ከተማ አስተዳደር የነዋሪዎች መታወቂያ ካርድ በህገወጥ መንገድ ከሦስት እስከ አራት ሺሕ ብር እየተሸጠ መሆኑን አዲስ ማለዳ ሰምታለች።

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ግለሰብ በቡራዩ ክፍለ ከተማ ከከተማ አስተዳደሩ መመስረት ጀምሮ የመታወቂያ ሽያጭ ተግባር በብዙ አካላት በሰፊው ሲፈጸም እንደነበር ገልጸዋል፡፡

አንድ ሰው መታወቂያውን ለማውጣት እስከ አራት ሺሕ ብር መክፈል አለበት ካሉ በኋላም፣ ክፍያውን ሳይፈም መታወቂያውን መውሰድ ግን የማይታሰብ ነው ሲሉ ጠቁመዋል፡፡

በህጋዊ መንገድ መታወቂያ ለማውጣት የሚሄዱ ነዋሪዎች ለወራት መመላለስ ስለሚሰለቻቸው ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ገንዘብ ከፍለው ለማውጣት ይገደዳሉም ነው የተባለው።

ሌላኛው ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ በከተማ አስተዳደሩ የመልካ ኖኖ ክፍለ ከተማ ነዋሪ እንዲሁ፣ ለብዙ ዓመታት በዚያው አካባቢ የኖሩ ሰዎች መታወቂያውን ለማውጣጥ በተደጋጋሚ ወደ ክፍለ ከተማው አቅንተው ማግኘት ሳይችሉ፣ ከሌላ አካባቢ የመጡ ነዋሪዎች ግን የመክፈል አቅም ስላላቸው ብቻ በአንድ ቀን ውስጥ መታወቂያው እንደሚሰጣቸው ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል፡፡

ህግን ባለተከተለ መንገድ የነዋሪነት መታወቂያው በገንዘብ የሚቸበቸበውም፣ ደላሎችና  የክፍለ ከተማ ውስጥ ያሉ ሠራተኞች በመናበብ ነው የተባለ ሲሆን፣ ደላሎች ሰዎችን ላመጡበት እንዲሁም የክፍለ ከተማው ሠራተኞችም መታወቂያውን ለሠሩበት ከሚገኘው ገንዘብ ድርሻቸውን እንደሚወስዱ ነው የተገለጸው፡፡

የገፈርሰ ጉጄ ክፍለ ከተማ ሌላ ነዋሪ እንዲሁ አሁን አሁን ድርጊቱ እጅግ ከመለመዱ የተነሳ በግለጽ የሚደረግ ተግባር ሆኗል ሲሉ ገልጸው፣ ወደ ክፍለ ከተማው በሚሄድበት ሰዓት ይህንኑ ጉዳይ ለማስፈጸም የመጡ ሰዎችን በብዛት ማየት የተለመደ ነው ብለዋል።

ነዋሪዎች መታወቂያውን በዚህ መልኩ ገንዘብ ከፍለው ከወሰዱ በኋላ፣ ለእድሳት በሚል በየሦስት ወሩ ሦስት መቶ ብር እንደሚጠየቁም ተጠቁሟል፡፡

በከተማ አስተዳደሩ መታወቂያ ሳይይዝ የሚንቀሳቀስ ሰው ከተገኘ ለእስር እንደሚዳረግ የገለጹት ነዋሪዎቹ፣ “መታወቂያውን እናውጣ ብለን ስንሄድ ደግሞ ይህን ያህል ብር አምጡ መባሉ እጅግ የሚያሳዝን ነው።” ሲሉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡

አክለውም “ይህ ሁሉ በግልጽ እና በአደባባይ ሲፈጸም መንግሥት ሳያውቅ ቀርቶ ነው ወይስ በአገሪቷ ሕግ የለም?” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

አዲስ ማለዳ ጉዳዩን አስመልክቶ ከሸገር ከተማ አስተዳደር ከንቲቫ ተሾመ አዱኛ ምላሽ ለማግኘት ያደረገችው ተደጋጋሚ ሙከራ ስልክ ባለማንሳታቸው ሳይሳካ ቀርቷል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply