
በሻሸመኔ ደብረ ስብሃት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን የሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅነት ተመድቤአለሁ የሚል ግለሰብ መምጣቱ ተገለጸ፡፡ አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ የካቲት 27 ቀን 2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ሸዋ የምእራብ አርሲ ሀገረ ስብከት መንበረ ጵጵስና በሆነው ደብረ ስብሃት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን የሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅነት ተመድቤአለሁ የሚል ግለሰብ መምጣቱ ተገለጿል፡፡ በሕገ ወጥነት ከተሾሙት “ኤጲስ ቆጶሳት” መካከል አባ ቻፒ ከተባለው ግለሰብ የተመደብኩ የሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ነኝ የሚል ግለሰብ በሻሸመኔ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ከመንግሥት ባለስልጣኖችና የጸጥታ ዘርፍ ኃላፊዎች ጋር በመሆን በቤተ ክርስቲያኑ መገኘታቸው ተገልጿል፡፡ ግለሰቡ በደብረ ሰብሃት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በመገኘት ነባር አገልጋዮች አገልግሎት እንዲሰጡ የማይመጡ ከሆነ እኛ እንመድባለን ማለታቸውንና የደብሩ አለቃ አባ ተስፋ ጊዮርጊስም ተቀብለው መመሪያውን እያስፈጸሙ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል። ነገር ግን ብፁዓን አባቶች የካቲት 25 ቀን 2015 ዓ.ም ከኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ጋር በተወያዩት መሠረት ቀጣይ ሳምንት የቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በአበው ሊቃነ ጳጳሳት ተባርኮ በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ለመክፈት ታቅዶ እንደነበረ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል ሲል ማኅበረ ቅዱሳን ብሮድካስት ዘግቧል፡፡
Source: Link to the Post