You are currently viewing በሽግግር ፍትሕ የፖሊሲ አማራጮች ላይ በ54 ከተሞች ምክክር ሊደረግ ነው  

በሽግግር ፍትሕ የፖሊሲ አማራጮች ላይ በ54 ከተሞች ምክክር ሊደረግ ነው  

በሃሚድ አወል

የፍትሕ ሚኒስቴር ትግራይ ክልልን ጨምሮ በአስራ አንዱም ክልሎች በሽግግር ፍትሕ የፖሊሲ አማራጭ አቅጣጫዎች ላይ በመጪው የካቲት ወር አጋማሽ ብሔራዊ ምክክር ማድረግ ሊጀምር ነው። ምክክሮቹን ከማካሄድ ጀምሮ የመጨረሻውን የፖሊሲ ረቂቅ እስከ ማዘጋጀት ድረስ ላለው ሂደት በድምሩ 89.3 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልገው ሚኒስቴሩ ያዘጋጀው ሰነድ አመልክቷል። 

የፍትሕ ሚኒስቴር “በኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ የፖሊሲ ማዕቀፍ አማራጮችን” የያዘ ሰነድ ለህዝብ ይፋ ያደረገው ከሶስት ሳምንት በፊት በታህሳስ ወር መጨረሻ ነበር። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሽግግር ፍትህ አማራጮች ላይ የሚያደርጋቸው ምክክሮች የሚመራበት ፍኖተ ካርታም በተከታይነት አዘጋጅቷል። ፍኖተ ካርታውን ያዘጋጀው ሚኒስቴሩ ለዚሁ ጉዳይ ያቋቋመው የባለሙያዎች ቡድን ነው።

በ20 ገጾች የተዘጋጀው እና “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው ይህ ፍኖተ ካርታ፤ ምክክር የሚካሄድባቸውን ከተሞች ዝርዝር፣ የተሳታፊዎችን ብዛት እና ረቂቅ የጊዜ ሰሌዳ ዘርዝሯል። ምክክሩ ከሚካሄድባቸው ከተሞች ዝርዝር ውስጥ በትግራይ ክልል የሚገኙት መቐለ፣ አዲግራት፣ አድዋ፣ ሽሬ እና አላማጣ ተካተዋል። 

ለምክክሩ ከተመረጡት ከተሞች ውስጥ በቁጥር ከፍ ያሉት የሚገኙት በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ነው። ባለፉት ዓመታት የጸጥታ ችግር ሲከሰትባቸው የነበሩ የወለጋ አካባቢዎችን ጨምሮ፤ በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ 13 ከተሞች ምክክሩን ያስተናግዳሉ። በተመሳሳይ ተደጋጋሚ ጥቃቶች እና የጸጥታ መደፍረስ ሲስተዋልባቸው የቆዩት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኙት የካማሺ እና መተከል ዞን ከተሞች የምክክሮቹ አካል ናቸው።

አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮችን ጨምሮ ይደረጋሉ በተባሉ 60 ምክክሮች፤ በድምሩ 3,500 ገደማ ተወያዮች እንደሚሳተፉ በፍኖተ ካርታ ሰነዱ ላይ ሰፍሯል። እስከ ግንቦት ወር በሚዘልቁት በእነዚህ ምክክሮች በእያንዳንዳቸው እስከ 60 ሰዎች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል። የምክክሩ ተሳታፊዎች የሚወያዩበት “የሽግግር ፍትሕ የፖሊሲ ማዕቀፍ አማራጮችን” የያዘው የፍትሕ ሚኒስቴር ሰነድ፤  የሽግግር ፍትሕ ውስጥ ሊካተቱ ይገባል ያላቸውን አላባዎችን የያዘ ነው። 

በሶስት ክፍሎች የተዋቀረው ይህ ሰነድ፤ ስለ ወንጀል ምርመራ፣ ክስ አመሰራረት፣ አጥፊዎችን ተጠያቂ ስለማድረግ፣ ስለ ምህረት፣ እርቅ እና ለተጎጂዎች የሚሰጥ ማካካሻ አማራጮችን አቅርቧል። ሰነዱ በእያንዳንዱ አማራጭ ስር ስጋት እና ጠንካራ ጎኖች ያላቸውን ሃሳቦችም አስፍሯል። ሰነዱን በተመለከተ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስተያየታቸውን የሰጡት ኔዘርላንድ በሚገኘው ዓለምአቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት አማካሪ የሆኑት አቶ ካሳሁን ሞላ፤ የፖሊሲ አማራጩ “በገለልተኛ ወገን ፍትህን ለመስጠት ወይም በኢትዮጵያ የተፈጸሙትን ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ረገጣዎችን በማጣራት እና ለህግ ለማቅረብ የማይፈቅድ ነው” ሲሉ ይተቻሉ።

የፍትሕ ሚኒስቴር ሰነድ አማራጮችን ከጠቆመባቸው ጉዳዮች መካከል አንደኛው “የፍርድ ሂደት በማን ይከናወን?” የሚለው ነው። የፍርድ ሂደትን በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤቶች ማከናወን “ከቅርብ ጊዜ ተሞክሮዎች እና ከሽግግር ፍትህ ግቦች አንጻር የሚመከር አማራጭ አይደለም” የሚለው የሚኒስቴሩ ሰነዱ፤ ቅይጥ ፍርድ ቤቶችም በተመሳሳይ “በሀገራችን የፖለቲካ ሁኔታ ተቀባይነት የሚኖራቸው አይደሉም” ሲል አስፍሯል።

የህግ ባለሙያው አቶ ካሳሁን፤ ሰነዱ ቅይጥ ፍርድ ቤቶችን ተቀባይነት እንደሌላቸው አድርጎ ማቅረቡ “የኢትዮጵያን ሁኔታ ችላ ያለ ነው” ይሉ። “ኢትዮጵያ በብሔር እና በፖለቲካ ተከፋፍላለች” የሚሉት አማካሪው፤ “ይህም ብሄራዊ የፍትህ ስርዓቱ ፍትህን ለማስፈን የሚፈለገውን አመኔታ እና ቅቡልነት ያሳጣዋል። እንዲሁም የክስ ሂደቱ ነጻ እና ገለልተኛ የመሆን እድሉ አነስተኛ ነው” ሲሉ ይሞግታሉ።

እንዲህ አይነት ሙግቶች የሚቀርቡበት የፍትሕ ሚኒስቴር ሰነድ፤ በመጀመሪያ ለውይይት የሚቀርበው በአዲስ አበባ ከተማ እንደሆነ በፍኖተ ካርታው ላይ ተመልክቷል። በአዲስ አበባ በሚደረጉት ምክክሮች የፌደራል እና የክልል መንግስታት ኃላፊዎች እንዲሁም ህግ አውጪዎች ይሳተፉበታል። ከዚህ በተጨማሪም ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እና ከዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ጋርም ምክክሮች እንደሚደረጉ ፍኖተ ካርታው ላይ ሰፍሯል።  

በአዲስ አበባ የሚደረጉት ምክክሮች መቋጫ ካገኙ በኋላ፤ በክልል ከተሞች የሚደረጉት ምክክሮች በመጋቢት ወር ላይ እንደሚጀምሩ በፍኖተ ካርታው የተካተተው የጊዜ ሰሌዳ ያሳያል። ከአዲስ አበባ ውጪ በ53 ከተሞች የሚደረጉት እነዚህ ምክክሮች በፍትሕ ሚኒስቴር በተቋቋሙ የባለሙያዎች ቡድን እንደሚመሩ የሚኒስትሮች ግብረ ኃይል ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዶ/ር ታደሰ ካሳ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

በምክክሮቹ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲን ለተወያዮች ማቅረብ እና የምክክሩን ቃለ ጉባኤ መያዝ የባለሙያዎች ቡድን አባላት ኃላፊነት መሆኑን ያነሱት ዶ/ር ታደሰ፤ የዩኒቨርሲቲ መምህራን በአጋዥነት እንደሚሳተፉ ገልጸዋል። ለዚህም ሲባል ከእያንዳንዱ ዩኒቨርሲቲ ስድስት መምህራን እንደሚመረጡ አክለዋል። ሁሉም ምክክሮች በቪዲዮ እንደሚቀረጹ ያነሱት ዶ/ር ታደሰ፤ ከምክክሮቹ መጠናቀቅ በኋላ ሙሉ ሪፖርት እንደሚዘጋጅ ጠቁመዋል።

የምክክሮቹ ዋና ዓላማ “ከፖለቲካ መዋቅሩ ሙሉ በሙሉ ነጻ ሆኖ መረጃን ከህዝቡ መሰብሰብ ነው” ሲሉ ፍትሕ ሚኒስቴር ባቋቋመው የባለሙያዎች ቡድን አባል የሆኑት ዶ/ር ታደሰ አብራርተዋል። ምክክሮቹን ለመምራት የተዘጋጀው የፍኖተ ካርታ ሰነድ በበኩሉ፤ የምክክሮቹ ዓላማ “በኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ሂደት አካላትና ተቋማዊ አደረጃጀቶች ላይ ግብዓቶችን፣ አመለካከቶችን እና ምኞቶችን ማሰባሰብ” መሆኑን ያትታል። 

ከምክክሮቹ የሚገኙት ግብዓቶች ከተሰበሰቡ እና ከተተነተኑ በኋላ፤ ዋና ዋና ግኝቶች፣ ሀሳቦች እና ግንዛቤዎች በሪፖርት ቅጽ ተጠቃለው ለቁልፍ ባለድርሻ አካላት እንደሚሰራጩ ፍኖተ ካርታው ያስረዳል። በተሰበሰበው ግብዓት ላይ በመመስረት የባለሙያዎች ቡድኑ “አጠቃላይ፣ የተቀናጀ እና አውድ-ተኮር የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ሰነድ” በግንቦት ወር መጨረሻ ያዘጋጃል ተብሏል። 

የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው ከተዘጋጀ በኋላ በባለድርሻ አካላት እንደሚገመገም በፍኖተ ካርታው ተመልክቷል። የሰነድ ረቂቁ ከተገመገመ በኋላ፤ የባለሙያዎች ቡድኑ የተሰጡ አስተያየቶችን አክሎ ፖሊሲው እንዲጸድቅ ለሚመለከተው አካል እንደሚያቀርብ ይጠበቃል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

The post በሽግግር ፍትሕ የፖሊሲ አማራጮች ላይ በ54 ከተሞች ምክክር ሊደረግ ነው   appeared first on Ethiopia Insider.

Source: Link to the Post

Leave a Reply