በቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት የሚመራው የኢጋድ የምርጫ ታዛቢ ቡድን ኬንያ ገባ

ዕረቡ ሐምሌ 27 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ የሚመራው የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) የምርጫ ታዛቢ ቡድን ትናንት ማክሰኞ ሐምሌ 26 ቀን 2014 ኬንያ መግባቱ ተገለጸ።

በኬንያ ሪፐብሊክ በቀረበለት ግብዣ መሰረት ታዛቢ ቡድኑ በአገሪቱ ውስጥ ሰላማዊ፣ ነጻ እና ተአማኒነት ያለው ምርጫ እንዲደረግ በገለልተኛነት ለመታዘብ ወደ ናይሮቢ ማቅናቱን ኢጋድ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ታዛቢ ቡድኑ በናይሮቢ በሚኖረው ቆይታ ከአገሪቱ ከከፍተኛ ባለስልጣናት፣ ከዋና ዋና የአገር አቀፍ እና አለም አቀፍ ባለድርሻ አካላት እንዲሁም ከሌሎች የምርጫ ታዛቢ ልዑካን ኃላፊዎች ጋር ጋር እንደሚወያይ ይጠበቃል።

የኢጋድ የአጭር ጊዜ የምርጫ ታዛቢ ቡድን ከቀጣናዊው ተቋም ስድስት አባል አገራት ማለትም ከኢትዮጵያ፣ ከኬንያ፣ ከሱዳን፣ ከደቡብ ሱዳን፣ ከጅቡቲ፣ ከሶማሊያ እና ከኡጋንዳ የተውጣጡ ሰባት ዋና እና 24 ጊዜያዊ አባላት የተዋቀረ ነው።

ከቋሚና ጊዜያዊ አባላቱ የተውጣጣና ቅድመ ምርጫ ግምገማን የሚያደርግ ቡድንም አካቷል።

ዶ/ር ሙላቱ በምርጫው የሚሳተፉትን ፖለቲከኞች ጨምሮ ሌሎችንም ከፍተኛ የኬንያ ባለስልጣናት አግኝተው እንደሚያነጋግሩም ኢጋድ በመግለጫው አስታውቋል።

ኢጋድ ከወር በፊት ከአፍሪካ ህብረት እና ከሌሎች ተቋማት ጋር በመቀናጀት ባደረገው የቅድመ ምርጫ ግምገማ የኬንያን ዝግጁነት ማድነቁ ይታወሳል።

የኢጋድ የምርጫ ታዛቢ ቡድን ተልዕኮ በመጪው ማክሰኞ በኬንያ ሪፐብሊክ የሚካሄደውን አጠቃላይ ምርጫ በብሔራዊ፣ ክልላዊ እና ዓለም አቀፋዊ የዲሞክራሲያዊ ምርጫ መስፈርቶች መሠረት ገለልተኛ፣ ተጨባጭ እና ተዓማኒ መሆኑን ግምገማ ማድረግ እንደሆነም ኢጋድ አስታውቋል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply