“በቀጠለው መንግስታዊ አፈናና ሽብር የፓርቲያችን አመራሮች የገቡበትን ማወቅ አልቻልንም።” ሲል እናት ፓርቲ ገለጸ። አሻራ ከአምስተርዳም እናት ፓርቲ ወደፖለቲካው ምኅዳር ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ…

“በቀጠለው መንግስታዊ አፈናና ሽብር የፓርቲያችን አመራሮች የገቡበትን ማወቅ አልቻልንም።” ሲል እናት ፓርቲ ገለጸ። አሻራ ከአምስተርዳም እናት ፓርቲ ወደፖለቲካው ምኅዳር ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ ትናንት በሄድንበት የመጠላለፍና የመጯጯህ ዘዬ ሳይሆን ሥነ ምግባርና ስክነት ባለው መንገድ ቢመራ ይህንንም እኛው አድርገነው እናሳይ በሚል መንግስት በየመዋቅሩ ያሉ አመራሮችንና አባላትን ሲያሥር በትዕግስትና በመግባባት ለመፍታት ጥረት አድርገናል ብሏል። የፖለቲካ ልክፍት አይለቅምና እንዲህ ያለው አካሄድ በመንግስት በኩል የተወደደ አይመስልም ሲል አክሏል። ከሰሞኑ በአማራ ክልል በቀጠለው መንግስታዊ አፈና:_ ፩. አቶ ሙሉጌታ የሺጥላ:- የሰቆጣ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ መምህር፣ የእናት ፓርቲ የሳይንት ፪ ምርጫ ክልል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እጩ ተወዳዳሪ፣ በሕልውና ዘመቻው ወጣቱን በማስተባበር በግንባር በመዋጋት እና በማዋጋት ጭምር ከፍተኛ ዋጋ የከፈለ ጀግና ነው። ሀገር ሰላም ስትሆን ደግሞ መልሶ በማስተማር ሥራው ተሠማርቶ እየተጋ እያለ የታፈነና ያለበት ኹኔታ የማይታወቅ። ፪. አቶ ታደለ ጋሸ:- በአዊ ዞን፣ ጓጉሳ ሽኩዴድ/ቲሊሊ/ከተማ የእናት ፓርቲ ም/ሰብሳቢ ሲሆን በቀን ፲፫/፱/፳፻፲፬ ዓ.ም ከባለቤቱ ዘንድ ክርስትና ለማስነሳት አንከሻ ጓጉሳ በሄደበት የታፈነና የት እንደገባ የማይታወቅ። ፫. አቶ ምግባሩ አስማረ:- የእናት ፓርቲ የሞጣ ምርጫ ክልል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እጩ ተወዳዳሪ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሠራተኛ፣ ባለ ትዳርና የ፪ ልጆች አባት ሲሆን በቀን ፲፮/፱/፳፻፲፬ ዓ.ም ከሚሠራበት ቦታ ታፍኖ ተወስዷል። ይህን ዜና ሥንጽፍ አባላችን ለጊዜው ሞጣ ፖሊስ ጣቢያ እንደታሰረ ማወቅ ችለናል። የታሠረበትንም ምክንያት አልተነገረም። ፬. ወ/ሮ ስመኝ ታደመ:- በወላይታ ዞን የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ አባልና ሶዶ አካባቢ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዕጩ ተወዳዳሪ ስትሆን በቀን ፲፮/፱/፳፻፲፬ ዓ.ም ከሥራ ቦታዋ የወሰዷትና ቤተሰብም መጠየቅ እንዳልቻለ ለማወቅ ችለናል። ወ/ሮ ስመኝ ከፍተኛ የሚባል በሀኪሞች የታወቀና ማሥረጃ የምታቀርብበት ሕመም ያለባት መሆኗ እየታወቀ ለኹለተኛ ጊዜ በአስቸጋሪ ኹኔታ ለእሥር የተዳረገች እህታችን ናት። ሀገርና ሕዝቧን ከመውደድ የዘለለ በደል የለባትም። ፓርቲያችን እኒህ አፈናዎች ፍጹም ፖለቲካዊና አምባገነናዊ ሥርዓትን ለማዋለድ የሚደረግ ነው ብሎ ያምናል። መንግስት እኒህን አመራሮቻችንን በጥርጣሬ ይዣቸዋለሁ ቢል እንኳ ያሉበትን ቦታ በማሳወቅ፣ ቤተዘመድ እንዲጠይቃቸውና ከሥጋት ነጻ እንዲሆን፣ ሕጋዊነትንና ሥርዓትን በተከተለ ወዲህም በ፵፰ ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት የመቅረብ መብታቸው ተከብሮ፣ ጠበቃ እንዲያቆሙ በመፍቀድ ማድረግ ሲኖርበት እንደ አሸባሪ ቡድን ሰዎችን መሰወር ማቆም እንዳለበት አጽንዖት ልንሰጥ እንወዳለን። በአመራሮቻችን ላይ እየደረሰ ያለውን ድርጊት እያወገዘ ከምርጫ ቦርድ፣ ከሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና መሰል ተቋማት ጋር በመሆን ሕጋዊ መንገድ ተከትሎ ጉዳዩን የሚከታተለው መሆኑን እየገለጽን መንግስት የዜሮ ድምር ፖለቲካዊ አካሄዱን በአፋጣኝ እንዲያርም በድጋሚ እንጠይቃለን ብሏል እናት ፓርቲ በመልዕክቱ።

Source: Link to the Post

Leave a Reply