አርብ ግንቦት 4 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) ከግል ጉዳዩ ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ ከተማ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስምንት ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት አለባቸው አሞኜን የገደለው የፖሊስ አባል በቁጥጥር ሥር መዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ።
ዋና ስራ አስፈፃሚው የዕለት ከዕለት ተግባራቸውን በማከናወን ላይ እንዳሉ ዛሬ ግንቦት 4/2015 ከጠዋቱ 4 ሰዓት ላይ በፖሊስ አባል መገደላቸውን ፖሊስ ገልጿል።
ግድያውን የፈፀመው በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የካሳንቺስ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት የቀጠና ኦፊሰር የሆነ አባል ሲሆን፤ የግል ጉዳዩ እንዲፈፀምለት ለወረዳው አስተዳደር ጽ/ቤት ያመለክታል፡፡
ወረዳው ጉዳዩን ተመልክቶ ምላሽ እንደሚሰጠው የተገለጸለት ቢሆንም ‹‹ጥያቄዬ እንዳይፈፀም የከለከልከው አንተነህ›› በሚል ምክንያት የወረዳውን ዋና ስራ አስፈፃሚ ቢሯቸው ውስጥ በስራ ላይ እንዳሉ በታጠቀው ሽጉጥ መግደሉ ታውቋል፡፡
ወንጀሉን የፈፀመው የፖሊስ አባል በቁጥጥር ሥር ውሎ ምርመራው እየተጣራ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል።የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፤ አለባቸው ‹‹በቢሮአቸው ቁጭ ብለው የህዝብ አገልግሎት በሚሰጡበት ወቅት የካዛንቺስ አካባቢ የማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት የቀጠና ኦፊሰር ባልደረባ ከሆነ አንድ ተገልጋይ በደረሰባቸው ጥቃት ህይወታቸው አልፏል።›› ብሏል።
አለባቸው በሥራ ቁርጠኝነት የሚታወቁ በበርካታ መንግስታዊና ህዝባዊ ተግባራት አርዓያነት ያለው ሥራ የሰሩና ያስተባበሩ አመራራች እንደነበሩ የገለጸው ክፍለ ከተማው፤ ጥቃት ያደረሰው ተጠርጣሪ በሕግ ቁጥጥር ሥር መዋሉን በመግለጽ፤ ተገቢውን የምርመራ ሂደት ተከትሎ ተጠያቂነት የማስፈን ሥራ እንደሚሰራ አስታውቋል።
The post በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የወረዳ 8 ዋናሥራ አስፈፃሚን የገደለው የፖሊስ አባል በቁጥጥር ሥር ዋለ first appeared on Addis Maleda.
Source: Link to the Post