በበጀት ዓመቱ ኃይል ለማመንጨት የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት የሚያስችል ውሃ ወደ ግድቦች እየገባ መሆኑ ተገለጸ

ሰኞ ነሐሴ 2 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በተያዘው የክረምት ወቅት ወደ ኃይል ማመንጫ ግድቦች እየገባ ያለው የውሃ መጠን በበጀት ዓመቱ ለማመንጨት የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት እንደሚያስችል የኃይል ማመንጫዎች ኦፕሬሽን ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት አስታወቀ።

በጽ/ቤቱ የፕላኒንግ ሥራ አስኪያጅ ጥሩወርቅ ሽፈራው እንደገለጹት፤ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች በሙሉ አቅማቸው ኃይል እንዲያመነጩ ለማድረግ ግድቦች በቂ ውኃ መያዝ ይኖርባቸዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ወደግድቦች እየገባ ያለው የውሃ መጠን በበጀት ዓመቱ ለማመንጨት የታቀደውን ለማሳካት እንደሚያስችል ታይቷል ብለዋል።

እስከ ሐምሌ 20 ቀን 2014 ድረስ በተሰበሰበው መረጃ መሰረት የአምስት ግድቦች የውሃ መጠን ከፍተኛ እንዲሁም የሦስቱ ደግሞ በቂ በሚባል ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ሥራ አስኪያጇ ጠቁመዋል።

በኹሉም ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች የቅድመ መከላከል ጥገናዎችን ከግድብ ውሃ አጠቃቀም ጋር አቀናጅቶ በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት በማከናወን የኃይል መቋረጥን ለመቀነስ እቅድ መያዙንም አመልክተዋል፡፡

በተያዘው ክረምት ከፍተኛ የውሃ መጠን ያከማቹ የማመንጫ ጣቢያዎች ከፍተኛ ኃይል እንዲያመነጩ በማድረግ አነስተኛ ውሃ የያዙ ግድቦች የሚኖራቸውን ጫና ቀንሶ ውሃ በተገቢው መጠን እንዲይዙ ለማድረግ መታቀዱን ሥራ አስኪያጇ ተናግረዋል፡፡

በለስ፣ ፊንጫ፣ ገናሌ ዳዋ 3፣ ግልገል ጊቤ 1ኛ እና አመርቲ ነሼ የውሃ ማመንጫ ጣቢያዎች የውሃ እጥረት ስለማያጋጥማቸው በሙሉ አቅማቸው ያመነጫሉ ተብሎ የታሰበ ሲሆን፤ በግቤ 3ኛ ማመንጫ ጣቢያ ግድብ ላይ በቂ ውሃ ለመያዝ ሲባል ጭነቱን በተወሰነ መልኩ ለመቀነስ መታሰቡንም ጠቁመዋል፡፡

በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በራስ አቅም የጥገና ሥራዎችን በማከናወን ለረጅም ጊዜ የቆሙ የተለያዩ ማመንጫ ጣቢያ ዩኒቶችን ወደ ኦፕሬሽን መመለስ እንደተቻለ ያስታወሱት ጥሩወርቅ፤ በተያዘው በጀት ዓመትም ተመሳሳይ ሥራዎችን በመስራት የማመንጫ ዩኒቶች በአግባቡ ኃይል እንዲያመርቱ ለማድረግ እና ተቋሙ ለጥገና ሥራ የሚያወጣውን ወጪ ለመቀነስ እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የማመንጫ ጣቢያዎችን የመለዋወጫ እቃ እጥረት ለመፍታትና በሙሉ አቅማቸው ኃይል እንዲያመነጩ ለማድረግ፤ የመለዋወጫ እቃዎችን በማዕቀፍ የግዥ ሥርዓት ለማከናወን እየተሰራ ካለው ሥራ በተጨማሪ፤ ለ11 ማመንጫ ጣቢያዎች የሚያገለግል የመለዋወጫ ዕቃ በቀጥታ ግዢ ለመፈፀም በሂደት ላይ እንደሚገኝ መናገራቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መረጃ አመላክቷል፡፡

የዘርፉን የኦፕሬሽንና የጥገና ሠራተኞች ክህሎት ለማሳደግ ዓለም አቀፍ ልምድ ያላቸውን ኩባንያዎች በአገር ውስጥ በማምጣት ለሠራተኞች ሥልጠና እንዲሰጡ ለማድረግ ዕቅድ መያዙንም ለማወቅ ተችሏል፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply