በባልደራስ አስተባባሪነትና ሀሳብ አመንጭነት የተጀመረው የአዲስ አበባ ራስ ገዝነት ጉዳይ ያገባናል ካሉ የተለያዩ ፓርቲዎች ጋር ውይይት ማካሄዱ ተገለፀ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ጥቅምት 1…

በባልደራስ አስተባባሪነትና ሀሳብ አመንጭነት የተጀመረው የአዲስ አበባ ራስ ገዝነት ጉዳይ ያገባናል ካሉ የተለያዩ ፓርቲዎች ጋር ውይይት ማካሄዱ ተገለፀ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ጥቅምት 11 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ በዛሬው እለት ጥቅምት 11 ቀን 2013 ዓ.ም ስድስት ኪሎ በሚገኘው በባልደራስ ዋና ጽ/ቤት በአዲስ አበባ ራስ ገዝነት ጥያቄ ዙሪያ ቀድሞ ቀጥሮ ከያዙት 6 ፓርቲዎች በተጨማሪ ሌሎች 3 ተካተው ውይይቱን አካሂዷል። ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ፊት አውራሪ ሆኖ እንዳስጀመረው የተገለፀው በአዲስ አበባ የራስ ገዝነት ጥያቄ ጉዳይ እንወያይ መድረክ ዛሬም በቀደመው መድረክ ያልተገኙ ፓርቲዎች በተገኙበት ተከናውኗል። የአዲስ አበባ ከተማ ህዝብ የራስ ገዝነት ጥያቄውን ተቀብሎ በባልደራስ 5ቱም ጽ/ቤቶች የፊርማ ድጋፍ ማካሄድ ከጀመረ ሰነባብቷል። በዛሬው ውይይትም ኢዲህ፣አብሮነት፣የኢትዮጵያ ብሄራዊ አንድነት ፓርቲ፣የኢትዮጵያ ተራማጅ ፓርቲ፣ባልደራስ፣አሲምባ፣አብን፣ኢዜማና ጋህፌዴን ስለመገኘቱ የገለፀው የባልደራስ ጋዜጠኛ ወግደረስ ጤናው ነው። በመጀመሪያው ዙር ምክክር ላይ የተሳተፈው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ(ኢዜማ) ዛሬም በ3 ተወካዮቹ በኩል የተገኘ መሆኑን የገለፀው ወግደረስ ነገር ግን በአዲስ አበባ ከተማ የራስ ገዝነት ጥያቄ ላይ ከያዘው አቋም በመንሸራተት አሁን ጊዜው አይደለምና ሌሎች ተጨማሪ ሀሳቦችን በመስጠት በሚቀጥለው የጋራ ውይይት ላይ እንደማይገኝ አስታውቋል ነው ያለው። በዛሬው የውይይት መድረክ የተሳተፈው የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄም (አብን) አዲስ አበባ በአፓርታይድ አገዛዝ ስር መሆኗን እንደሚያምን በመግለፅ ሀሳቡን እንደሚስማማበት አስታውቋል ያለው ወግደረስ የጋራ ኮሚቴ የማቋቋምን ጉዳይ በተመለከተ ግን ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል ሲልም አክሏል። ባልደራስ ዛሬ የአዲስ አበባን የራስ ገዝነትን ጉዳይ በተመለከተ የጋራ አቋም ካላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ኮሚቴ እንዲዋቀር ጠይቋል። ተጨማሪ ጊዜ አስፈላጊ መሆኑ ስለታመነበት ከ2 ሳምንት በኋላ ውይይቱ እንዲቀጥል ስምምነት ስለመደረሱ ነው ከወግደረስ ጋር የነበረን ቆይታ ያመለከተው።

Source: Link to the Post

Leave a Reply