በቤልጅዬም የኢትዮጵያ ኤምባሲ ስለቀረበው የሥዕል ትርዒት

በቤልጅዬም የኢትዮጵያ ኤምባሲ ስለቀረበው የሥዕል ትርዒት

አገኘሁ_አዳነ_ድልነሣሁ-

በቤልጅዬም የኢትዮጵያ ኤምባሲ፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አለ_የሥነጥበብና_ዲዛይን_ት_ቤት ጋር በመተባበር በቤልጅዬም ከየካቲት 18 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ የሥዕል ትርዒት አቅርበዋል። ይህ ኤግዚቢሽን መልኩና ፈርጁ ብዙ የሆነውን የዲፕሎማሲ ዓለም በሥነጥበብና ባህል ለማዋዛት፣ ነባሩ የሥነ ጥበብ ብሂል በዘመነኛው የሥነ ሥዕል እንቅስቃሴ ላይ ያሳደረውን ክንደ ብርቱ ተፅዕኖ ለማመላከትና ት/ቤቱ ከቀረው ዓለም አቻ ተቋማት ጋር ትስስር መፍጠር እንዲችል ታስቦ የተሰናዳ ነበር።  በትርዒቱ መክፈቻ የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ግንኙነት  ቢሮ ዋና ፀሐፊ ስቴፋኖ ሳኒኖ (Stefano Sannino)፣ የቤልጂየም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተወካይ፣ አምባሳደር  ባርት ዴ ግሩፍ፣ የአካፓድ ምክትል ዋና ፀሐፊ ዶ/ር ኖርበርት ሪቻርድ ኢብራሂም፣ በብራስልስ የሚገኙ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት የተገኙ ሲሆን፣ የሥነ ጥበብ ልሂቃንና የሥነ ጥበብ አፍቃርያን ታድመውበታል።
በቤልጅዬም የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባለሙሉ ስልጣን እንደራሴ አምባሳደር ሒሩት ዘመነ፣ አምባሳደር ሞላልኝ አስፋው እና የሥራ ጓዶቻቸው ዝግጅቱ የተሳካ ይሆን ዘንድ የሚያስመካ ጥረት አድርገዋል። ጥረቱ ፍሬ አፍርቶም በቤልጅዬም የሚገኙ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ፣ የታሪክ፣ የሂስ እና የሥነጥበብ ንድፈ ሐሳብ ልሂቃን በኤምባሲው እንዲሰበሰቡ ሆነዋል።
የአንትወርፕን (Antwerpen) Royal Academy of the Arts መምህራንም በኤምባሲው ተገኝተው ፍሬ ያለው ውይይት ማድረግ ችለናል። ምሑራኑ ትርዒቱን ተመልከተው መደነቃቸውን የገለጹልን ሲሆን፣  በምንተባበርባቸው ተቋማዊ የጋራ ጉዳዮች ላይ መክረናል።  
የቀረበው የሥዕል ትርዒት ተወዳጅነቱ ከፍ በማለቱ ምክንያት ለተጨማሪ አንድ ሳምንት የተራዘመ ሲሆን፣ ለአካባቢው ማኅበረሰብ መነቃቃት መፍጠሩን በዝግጅቱ አካል የሆንነው ሙያተኞች መታዘባችንን እንመሰክራለን።
ሀገራችን ኢትዮጵያ ከሌላው ዓለም ጋር የምትነጋገርበትን የቋንቋ አማራጭ ለማስፋት ሥነጥበብን ወደ ዲፕሎማሲው ዓለም የጋበዙትን አምባሳደር ሒሩት ዘመነን፣ አምባሳደር ሞላልኝ አስፋውንና የሥራ ጓዶቻቸውን  ማመስገን ይገባል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply