በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ጉዳት ለደረሰባቸው ትምህርት ቤቶች ለመልሶ ግንባታ ገቢ ለማሰባሰብ መታቀዱ ተሰምቷል፡፡

በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል 280 የሚሆኑ ትምህርት ቤቶች በግጭት ምክንያት ጉዳት እንደደረሰባቸው የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታውቋል፡፡
በክልሉ ጉዳት ለደረሰባቸው ትምህርት ቤቶች መልሶ ለመገንባት እና ለተማሪዎች ምቹ ለማድረግ፣ በክልሉ ዋና ከተማ አሶሳ እና በአዲስ አበባ የገቢ ማሰባሰቢያ መድረኮች ለማከናወን መታቀዱን የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር ምትኩ ዘነበ ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡

በመተከል እና በካማሺ ዞን ስር በሚገኙ ወረዳዎች በአብዛኛው ትምህርት ቤቶች መውደማቸውን ጠቁመው፤ከመዋለ ህጻናት እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በከፊል ጉዳት ሲደርስባቸው ሙሉ በሙሉ የወደሙ መኖራቸውንም ሃላፊው ተናግረዋል፡፡

በክልሉ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ጉዳት ቢደርስባቸውም የትምህርት ስርአቱ እንዲቀጥል በተቻለ መጠን ጥረት መደረጉን የሚናገሩት ሃላፊው፣በአሁኑ ወቅት ተማሪዎችም ትምህርታቸውን እየተከታተሉ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

ትምህርታቸውን እየተከታተሉ የሚገኙት ግን የመሰረተ ልማት ባልተሟላበት ሁኔታ ውስጥ መሆኑን ገልጸው፣እነዚህን ጉዳት የደረሰባቸውን ትምህርት ቤቶች ለተማሪዎች ምቹ ለማድረግ ገቢ ለማሰባሰብ መታቀዱን ገልጸዋል፡፡
የገቢ ማሰባሰቢያው ጊዜና የሚያስፈልገው መጠን ምን ያህል እንደሆነ በቅርብ ጊዜ ይፋ እንደሚደረግ ሃላፊው ተናግረዋል፡፡

በእሌኒ ግዛቸው

ጥር 24 ቀን 2016 ዓ.ም

Facebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Source: Link to the Post

Leave a Reply