በቤንች ሸኮ ዞን የጉራ ፈርዳ ተፈናቃዮች የመጠለያ እና የውሀ አቅርቦት ችግራቸው እንዲፈታላቸው ጠየቁ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ህዳር 19 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ አበ…

በቤንች ሸኮ ዞን የጉራ ፈርዳ ተፈናቃዮች የመጠለያ እና የውሀ አቅርቦት ችግራቸው እንዲፈታላቸው ጠየቁ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ህዳር 19 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ በደቡብ ክልል ቤንች ሸኮ ዞን ከጉራ ፈርዳ ወረዳ የሸኮ ታጣቂዎች በፈፀሙት ጥቃት የተፈናቀሉ ወገኖች ወደ ወረዳው ዋና ከተማ ቢፍቱ መሸሻቸው ይታወቃል። በመንግስት መዋቅር ውስጥ ባሉ በርካታ አመራሮች ሳይቀር ድጋፍ እንዳላቸው የሚነገርላቸው የሸኮ ታጣቂዎች ጥቅምት 8ለ9 እና ጥቅምት 10ለ11 ሌሊት በሹፒ እና አሮጌ ብርሀን ቀበሌዎች በፈፀሙት አሰቃቂ ማንነት ተኮር የጅምላ ጥቃት ከ40 በላይ አማራዎች ስለመገደላቸው፣ በርካቶች ስለመቁሰላቸውና በሽህዎች የሚቆጠሩ ወገኖችም ስለመፈናቀላቸውና መዘረፋቸው ተዘግቧል። በጉራ ፈርዳ ወረዳ በቢፍቱ ከተማ በአንድ ት/ቤት ተጠልለው ከሚገኙ ተፈናቃዮች መካከል አቅም ያላቸው በግል የመኖሪያ ቤት የተከራዩና ከፊሎችም ወደ ዘመድ የተጠጉ ሲሆን አሁንም ግን ከ500 በላይ የሚሆኑት በት/ቤት ተጠልለው ይገኛሉ። በየወሩ የተወሰነ እርዳታ እንደሚደረግላቸው ቢገለፅም እርዳታው ግን በቂ አለመሆኑ እየተነገረ ነው። በት/ቤት የተጠለሉት ተፈናቃዮችም ወደ ከተማ ገብተው ቤት ተከራይተው ለመኖር የሚያስችል ገንዘብም ሆነ በቅርብ የሚደግፋቸውና የሚያስጠልላቸው ዘመድ አለማግኘታቸው ተገልጧል። ተፈናቃዮች ት/ቤቱ ወደ መደበኛ አገልግሎቱ ሲመለስም የእኛ እጣ ፈንታ ምን ይሆናል የሚል ስጋት አድሮባቸዋል። ከሰሞኑም ታንከር ተበላሽቷል በሚል ከውሀ አቅርቦት ጋር በተያያዘ የገጠማቸውን ችግርም መንግስትም ሆነ የሚመለከታቸው አካላት እንዲፈቱላቸው ጠይቀዋል። በቤንች ሸኮ ዞን የጉራ ፈርዳ ወረዳ አስተዳደር ጽ/ቤት ኃላፊ እና የተፈናቃዮች አስተባባሪ ለሆኑት ለአቶ ደበላ ጋቢሳ ስለተፈጠረው ችግር ለማጣራት ብንደውልም በአካል ካልመጣችሁ መረጃ አልሰጥም በማለት ሳይተባበሩን ቀርተዋል። በሌላ መረጃ በአሮጌ ብርሀን ቀበሌ ህዳር 17 ቀን 2013 ዓ.ም ምሽት ላይ ታጣቂዎች በአንድ የአካባቢው ነዋሪ በሆኑ አማራ ላይ በጥይት ግድያ ስለመፈፀማቸው ተገልጧል። ፎቶ:ፋይል

Source: Link to the Post

Leave a Reply