በቦረና ወረዳ መካነ ሰላም ከተማ ላይ በሽህዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች በተገኙበት ህዝባዊ ስብሰባ ተካሂዷል፤ በፈርጣጮች የታሰሩ ሰልጣኝ ፋኖዎች በአስቸኳይ እንዲፈቱ ተጠይቋል። አማራ ሚዲያ ማዕከል…

በቦረና ወረዳ መካነ ሰላም ከተማ ላይ በሽህዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች በተገኙበት ህዝባዊ ስብሰባ ተካሂዷል፤ በፈርጣጮች የታሰሩ ሰልጣኝ ፋኖዎች በአስቸኳይ እንዲፈቱ ተጠይቋል። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ግንቦት 5 ቀን 2014 ዓ.ም… አዲስ አበባ ሸዋ ከአሳሪዎች ጋር እንተዋወቃለን፤ ፈርጣጮች ናቸው የሚሉት በደቡብ ወሎ ዞን የመካነ ሰላም ከተማ ነዋሪዎች መስተዳድሩ ከሰሞኑ ሰልጣኝ ፋኖዎችን በጅምላ ማሰሩ ማንአለብኝነት፣ ጸረ አማራነት እና ተላላኪነት ነው ይላሉ፤ ይህን ፋኖን የማሳደድ ሞራል ከየት እንዳገኙት አይገባነም ሲሉም አክለዋል። ከቀናት በፊት በአካል ብቃት እንቅስቃሴ ላይ እያሉ በጅምላ ከታሰሩ በርካታ ፋኖዎች መካከል 21 የሚሆኑት እንዳልተፈቱ ለአማራ ሚዲያ ማዕከል (አሚማ) ተናግረዋል። እነዚህ ፋኖዎች በአስቸኳይ እንዲፈቱ ግንቦት 4/2014 በሰላማዊ ሰልፍ ጠንካራ መልዕክታቸውን ካስተላለፉት ወጣቶች በተጨማሪ ከ3 ሽህ ያላነሰ ህዝብ በመካነ ሰላም 02 ቀበሌ አዳራሽ በነበረው ስብሰባ ላይ ተገኝቶ መጠየቁን አውስተዋል። ስብሰባውን የመሩት የመካነ ሰላም ከተማ እና የገጠር ወረዳ አስተዳድር አመራሮች ሲሆኑ በመድረኩ 4 ጉዳዮች በዋናነት ተነስተዋል። 1) ለምን ሰለጠናችሁ በሚል በገፍ የታሰሩ ፋኖ ልጆቻችን ይፈቱ፣ ስልጠና እንዳይኖር ታግዷል የሚለው አይሰራም። 2) የውሃ ችግር በአስቸኳይ ይስተካከልልን። 3) ከእምነት ተቋማት አያያዝ አኳያ ያላችሁን ቁመና አስተካክሉ። ሙስሊም እና ክርስቲያን አንድ ነው አትከፋፍሉን አታለያዩን በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል። በተለይም አንድን ስፍራ ለገብርኤል ቤተ ክርስቲያን፣ ለሙስሊም መቃብር እንዲሁም ደን ነው በሚል ለ3 ወገኖች ደብተር መስጠት በግጭት ለመነገድ እንደሆነ ይገባናል ብለዋል፤ እንዲስተካከልም ጠይቀዋል። አመራሮቹም ለ3 አካላት ስለተሰጠው ስፍራ ጉዳዩ በፍ/ቤት የተያዘ ስለሆነ ፍ/ቤት ያጣራዋል ስለመባሉ እንዲሁም ፋኖዎችን እንደሚፈቷቸው ቃል ገብተው ስለመውጣታቸው ተነግሯል። በመድረኩ የተገኙ የሀገር ሽማግሌዎች፣የሀይማኖት አባቶች እና ወጣቶችም የሚፈጠሩ ክፍተቶች ካሉ በራሳቸው እንደሚፈቷቸው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ጉዳዩ የሁላችን መሆኑን ለማሳየትም “በፋኖ ስም የታሰረው የመካነሰላም ወጣት ብቻ አይደለም፤ ከትናንት ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ እስር ላይ ያለው ፋኖነት የሚባለው የአያቶቻችን እሴት ነው፤ መካነሰላም ላይ ፋኖነት ሲታሰር ደግሞ ሁሉም ፋኖ ታስሬያለሁ ብሎ ወንዝ ሳይከልለው ሊጮህ ይገባል፤ ፋኖነት ታስሯልና የድፍን ወሎ አማራ ፋኖ ብቻ ሳይሆን የጎንደር የሸዋው የጎጃሙ ፋኖም ሊቆጣ ግድ ነው።” የሚል አስተያየት በማህበራዊ ሚዲያ ሲቀባበሉት ተመልክተናል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply