በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች የተፈፀሙ ዘር ተኮር እና ሌሎች ሰብዓዊ ጉዳት ያስከተሉ ጥቃቶችን የሚመረመር ገለልተኛ አጣሪ ኮሚሽን በአስቸኳይ እንዲቋቋም ሲል የኢትዮጵያዊያን ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ(…

በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች የተፈፀሙ ዘር ተኮር እና ሌሎች ሰብዓዊ ጉዳት ያስከተሉ ጥቃቶችን የሚመረመር ገለልተኛ አጣሪ ኮሚሽን በአስቸኳይ እንዲቋቋም ሲል የኢትዮጵያዊያን ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ(…

በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች የተፈፀሙ ዘር ተኮር እና ሌሎች ሰብዓዊ ጉዳት ያስከተሉ ጥቃቶችን የሚመረመር ገለልተኛ አጣሪ ኮሚሽን በአስቸኳይ እንዲቋቋም ሲል የኢትዮጵያዊያን ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ(ኢዴፓ) ጠየቀ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ህዳር 16 ቀን 2013 ዓ.ም… አዲስ አበባ ሸዋ “ንፁሃንን በመግደል የፖለቲካ ትርፍ አይገኝም!” ያለው የኢትዮጵያዉያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ( ኢዴፓ )በወቅታዊ ጉዳይ በሰጠው መግለጫ በአገራችን ኢትዮጵያ በ2010 ዓ.ም በህዝብ ተቃውሞና እምቢተኝነት ከመጣው የለውጥ አጋጣሚ ማግስት ጀምሮ እየታየ የነበረው የፖለቲካ አለመረጋጋት አሁንም እንደቀጠለ ነው ብሏል፡፡ ኢዴፓ በአገራችን እየተስተዋለ የሚገኘው የፖለቲካ ውጥረት ተገቢ ትኩረት ተሰጥቶት መፍትሄ ማግኘት ካልቻለ የአገራችን ህልውና አደጋ ውስጥ ሊወድቅ እንደሚችል ያለውን ስጋት በተደጋጋሚ ሲገልፅ ቆይቷል ነው ያለው፡፡ ለችግሩ መባባስም የአመራር ድክመት እና ከራስ ውጭ የሌሎችን አማራጭ ሃሳብ የገፊነት አካሄድ ስለመሆኑም ፓርቲው ገልጧል። አሁን አገራችን ለተጋረጠባት ዘርፈ ብዙ ችግሮች መፍትሄ የሚሆነውም ሁሉን አቀፍ የሆነ የእርቅና የሽግግር መንግስት ሲቋቋምና ለዚህም የሚረዳ አገር አቀፍ የውውይት መድረክ ሲፈጠር መሆኑን ኢዴፓ ከኢሀን እና ህብር ፓርቲ ጋር ሆኖ በአብሮነት በኩል አማራጭ መፍትሄ አቅርበናል ያለው ፓርቲው እንዲያውም እንዴት ተግባራዊ ሊሆን እንደሚችል የሚያሳይ ዝርዝር የሽግግር ሰነድ በማዘጋጀት ጭምር ለተጋረጠብን አደጋ መውጫ መንገድ አመላክተናል ሲል አስታውቋል፡፡ ነገር ግን ይሄን ሰነዳችንን ከቡድናዊነት፣ ከስልጣን ጥማትና ከጥላቻ በመነጨ ያልሆነ ትርጉም በመስጠት የፖለቲካ መሪዎቻችን ሳይቀበሉት ቀርተዋል ያለው ኢዴፓ በዚህ ምክንያትም የአገራችን የፖለቲካ ውጥረት ተባብሶ አሁን የምንገኝበት መስቀለኛ መንገድ ላይ እንድንገኝ ተገደናል፤ በዜጎቻችን ላይም ከዕለት ወደ ዕለት የፍርሃት እና የስጋት ድባብ እንዲያጠላ ሆኗል ብሏል፡፡ በሰላም ወጥቶ መግባትና እንደልብ ከአንዱ ክልል ወደ ሌላኛው ክልል ተዘዋውሮ ሃብት ንብረት የማፍራትና በነፃነት የመንቀሳቀስ ህገ-መንግስታዊ መብት አደጋ ላይ ወድቋል ብሏል፤ በተጨማሪም የህወሃት እና የብልፅግና ውጥረት ለይቶለት ወደ ጦርነት ውስጥ ስለመገባቱ ገልጦ አውዳሚ ጦርነት እየተካሄደ ባለበት ሁኔታም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎችም ዘርን መሰረት ያደረገው የዘር ጭፍጨፋ ተባብሶ ስለመቀጠሉ አስታውቋል፡፡ በቅርቡ በማይካድራ በዜጎች ላይ የደረሰውን ጭፍጫፋ ሰምተን ሃዘናችን ሳይጠግን ሰሞኑን ደግሞ በቤንሻንጉል ጉሙዝ እና በኮንሶ አማራ በመሆናቸው ብቻ ወገኖቻችን ላይ መጠነ ሰፊ የዘር ጭፍጨፋ ስለመካሄዱ የገለፀው ኢዴፓ በዚህም ምክንያት የብዙ ንፁሃን ዜጎች ህይወት አልፏል፣ የአካል ጉዳት ሰለባ ሆነዋል፣ ቤት ንብረታቸው ተቃጥሏል፣ ተዘርፏል እንዲሁም በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል ብሏል። ጥቃቱ በተፈፀመበት አካባቢ ላይ የሚገኙ ከጥቃቱ የተረፉ ዜጎችም ለተጨማሪ ጥቃት ተጋላጭ በመሆናቸው የድረሱልኝ ጩኸት እያሰሙ መሆናቸው መረጃዎች እየደረሱን ነው ያለው ፓርቲው በዚህ ጥቃት ኢዴፓ የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን እየገለፀ ለሟች ቤተሰቦች እና ወዳጅ ዘመዶች መፅናናትን ይመኛል ብሏል፡፡ የኢዴፓ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች ላይ እየተፈፀሙ ባሉ ዘር ተኮር ጥቃቶች ዙሪያ ሰፊ ውይይት ካደረገ በኋላ የሚከተለውን አቋም መውሰዱን አስታውቋል። መንግስት በማይካድራ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ እና በኮንሶ በጥቃቱ ሰለባ የሆኑ ዜጎች መልሰው የሚቋቋሙበትንና ተገቢውን ካሳ የሚያገኙበትን ሁኔታ በፍጥነት እንዲያመቻች፣ ጉዳዩን ወደ ተለያዩ አካላት ማላከኩን በመተው ህግ የማስከበሩን ሃላፊነት በአግባቡ እንዲወጣ፣ በየክልሉ አሁንም በአደጋ ውስጥ ያሉ ዜጎች ላይ ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስ አስፈላጊውን ከላላ እና ጥበቃ እንዲያደርግ ሲል አሳስቧል። በጥቃቱ ውስጥ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ እጃችው ያለበትን አካላት ተከታትሎና አጣርቶ ለፍርድ በአስቸኳይ እንዲያቀርብ የጠየቀው ኢዴፓ በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተለያዩ የአገራችን ክልሎች የተፈፀሙ ዘር ተኮር ጥቃቶችን እና ሌሎች ሰብዓዊ ጉዳት ያስከተሉ ጥቃቶችን የሚመረመር ገለልተኛ አጣሪ ኮሚሽን በአስቸኳይ እንዲቋቋም አሳስቧል። የኢትዮጵያ ህዝብም እንደዚህ አይነት እኩይ ተግባር የሚፈፅሙ አካላት መጠቀሚያ ሳይሆን ድርጊቱን አጥብቆ በመቃወም ወገኖቹን ከጥቃት መከላከል አለበት፡፡ አንድነታችንን፣ አብሮነታችንንና መቻቻላችንን የሚጎዱ ማንኛቸውም ድርጊቶች በመከላከል አንድነቱን ይበልጥ ሊያጠናክር ይገባል ሲልም መክሯል፡፡ ለዚህ ሁሉ ተደራራቢ ቀውስ የተዳረግነው በመንግስት የአመራር ድክመት እና ከራሱ ውጭ የሌሎችን አማራጭ ሃሳብ ገፊ በሆነው ግትር ባህሪው ስለሆነ ሁሉን አቀፍ እና አካታች የሆነ የእርቅና የሽግግር መንግስት የሚቋቋምበት ሁኔታ መፈጠር አለበትም ብሏል፡፡ በዚህም ላይ የሚመክር አገር አቀፍ የውይይት መድረክ እንዲመቻች፣ ለውይይቱም ስኬታማነት በፖለቲካ አቋማቸው ምክንያት በእስር ላይ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በአስቸኳይ እንዲፈቱም ጠይቋል። በመጨረሻም የአገር ሽማግሌዎች፣ የእምነት ተቋሞች፣ ሃላፊነት የሚሰማችሁ አክቲቪስቶች፣ ሙሁራን፣ ሲቪክ ተቋማት፣ የመንግስት እና የግል የሚዲያ ተቋማት አገራችን ከማንነት ተኮር ጥቃት ወጥታ አንድነታችን የሚጠናከርበትን መንገድ በማመቻቸት ተግባራዊ ሃላፊነታችሁን እንድታበረክቱ ሲል ኢዴፓ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply