
በታሪካዊው ቴአትር ቤት ታሪካዊ ስህተት ሊሰራ ይሆን…? ጋዜጠኛ የኋላእሸት ዘሪሁን ********************************************* በመጪው ሃሙስ ማለትም የካቲት 23 /2015 ዓም 127 ኛ ጊዜ የሚከበረውን የዓድዋ ድልን በዓል ምክንያት በማድረግ በሃገር ፍቅር ቴአትር ቤት እለቱን የሚዘክር ቴአትር እየተዘጋጀ መሆኑን ሰምቼ ሳላበቃ አፍታም ሳልቆይ ሌላ አሳዛኝ ዜና ሰማሁ ። ጉዳዩንም ለማጣራትም ይመለከታቸዋል የሚባሉት ሁሉ ጋር ደወልኩ ። ነገሩ እውነት መሆኑንም አረጋገጥኩ። በአዲስ አበባ ባህል ፣ ኪነጥበብ ቱሪዝም ቢሮ ስር የሚገኙት አራቱም ቴአትር ቤቶች ማለትም (የኢትዮጵያ ሃገር ፍቅር ቴአትር፤የአዲስ አበባ ቴአትር እና ባህል አዳራሽ፤ራስ ቴአትር ፤የህፃናት እና ወጣቶች ቴአትር )ሲሆኑ በፌዴራሉ የባህል እና ስፖርት ሚንስቴር ስር የሚገኘው የኢትዮጵያ በብሔራዊ ቴአትር ሲሆን በተጨማሪም ከየክፍለ ከተማው የተውጣጡ በአጠቃላይ 535 ባለሞያዎች የተሳተፉበት በታሪክ ጭምር የሚያስጠይቅ እና አንገት እሚያስደፋ ሙዚቃዊ ተውኔት ሊቀርብ መሆኑን ሰማሁ ። ደግሞም አረጋገጥኩ። ነገሩ እንዲህ ነው … ” ከበላይ የመጣ ትዕዛዝ ነው ” በሚል ” የዓድዋ ድል በዓል እስከዛሬ ባለቤት አልነበረውም ። ከዚህ በኋላ ግን መከላከያ ሚኒስቴር በባለቤትነት ይይዘዋል ” በሚል ትዕዛዝ በቴአትር ቤቶቹ ተወካዮች አማካኝነት ሃገር ፍቅር ቴአትር ቤት አዳራሽ ውስጥ ለተሰበሰብት ባለሞያዎች የአዲስ አበባ ቴአትር እና ባህል አዳራሹ ስራ አስኪያጅ በአቶ ካሳዬ ገበየሁ አማካኝነት ይነገራቸዋል። በመቀጠልም እሚቀርበው ሙዚቃዊ ተውኔት ላይ አፄ ሚኒሊክን ፣እቴጌ ጣይቱ ፣የጦር አበጋዞቻቸው፣የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ፣ የዓድዋ ጦርነት ወቅትን የሚገልጹ አልባሳት እና ጌጣጌጥ ፣ ጦርነቱ የተካሄደባቸውን ቦታዎች ፈፅሞ በሙዚቃዊ ትያትሩ ላይ መገለጽ እንደሌለባቸው ይነገራቸዋል ። ለተውኔቱም አዘጋጅ ይመረጥ ይባል እና ተሻለ ወርቁ ይመረጣል ። እሱም ለመስራት ፈቃደኛ ይሆናል ። ልብ አድርጉልኝ ይህ ስራ የተፃፈ ተውኔት የለውም ። ለሙያ ያለ ንቀት ከዚህ ይጀምራል ። ያለ ፅሁፈተ ተውኔት ምን አይነት የመድረክ አቅርቦት እንደሚሰራ ባለሞያዎች የሆናችሁ አስቡት ። ነገሩ ምን ያህል ኮሚክ እንደሚሆንባችሁ እረዳለሁ ። በእርግጥ ይህን መሰሉ የግብር ይውጣ አካሄድ በተለይም ”ሙዚቃዊ ተውኔቶች” እየተባሉ በመንግሥት ትዕዛዝ በተለያየ ጊዜ በሚቀርቡ የይድረስ ይድረስ ስራዎች (የከተፋ ስራዎች ) የተለመዱ ናቸው ። ወደ ዋናው ጉዳዬ ስገባ አዘጋጅ ተመረጦ ወደ ስራው ከመገባቱ በፊት የስራው ተሳታፊ ባለሞያዎች የጥያቄውን መዓት ያዥጎደጉዱት ጀመር ። የታሪኩ ፊት አውራሪዎች በሌሉበት ምን ብለን ነው ስለ አድዋ የምንሰራው?፣ይሄንን የመሰለ የታሪክ ክህደት ለምን አስፈለገ? ወዘተ …ጥያቄዎች አቀረቡ ። አዘጋጁን ጨምሮ ከላይ የጠቀስኩት የማዘጋጃው ስራ አስኪያጅ ጭምር ቁጣ በተቀላቀለበት መንገድ ”ጥያቄ አናስተናግድም” ያሉ ሲሆን። ”ነገሩ እየገፋ ከመጣ ስራ እንዳይሰራ ሊያደርግ ይችላል ” በማለት ጉዳዩን ወደ በላይ ሃላፊዎች በማሳወቅ በወቅቱ ጥያቄ የጠየቁ 11 ባለ ሞያዎችን ከአዲስ አበባ ባህል ፣ ኪነጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ የመጡ የስራ ሃላፊዎች ለብቻ ጠርተው አናግረዋቸዋል ። (ያው ለብቻ ጠርቶ ማናገር ምን እደሆነ ይገባችኋል ) በወቅቱ የተገኙትም የቢሮ ሃላፊዎች ሰርፀ ፍሬ ስብሃት የኪነጥበብ ምክትል የቢሮ ሃላፊ፣አቶ አስፋው የባህል ዘርፍ ምክትል የቢሮ ሃላፊ እንዲሁም አቶ ፈይሳ የተሰኙ የዋናዋ የቢሮ ሃላፊ የዶክተር ሂሩት ካሳው የፅህፈት ቤት ሃላፊ ናቸው። እኔም ይሄንን ጉዳይ ዛሬ የካቲት 19/2015 ዓም ነገረ ኪን ለተሰኘው በትርታ 97.6 ሬዲዮ ዘወትር እሁድ ከ 6 ሰዓት እስከ 8 ሰዓት ለሚቀርበው ፕሮራሜ ግብአት ይሆነኝ ዘንድ ስለ ነገሩ ለማጣራት በመጀመሪያ ለ አቶ ሰርፀ ፍሬ ስብሃት ደውዬ የነበ ሲሆን ስልካቸው ዝግ ሆኖብኛል። በመቀጠል የማዘጋጃ ቴአትር ስራ አስኪያጅ አቶ ካሳዬ ገበየሁ ጋ በመደወል ስለ ጉዳዩ ጠይቄያቸው የነበረ ሲሆን ‘ከላይ በመጣ ትዕዛዝ ” ተውኔቱን እየሰሩት እንደሆነ ገልፀውልኝ የዓድዋን አዝማቾች ብሎም በወቅቱ የነበረውን እውነታ ሳያነሱ እንዴት ያለ ተውኔት ይሰራል ? ይሄ ነገር ከታሪክ ጋርስ አያጋጭም ወይ ? ብዬ ለጠየቅኳቸው ጥያቄ ምላሽ ሊሰጡኝ እንደማይችሉ እና እርሳቸው በነገሩ አምነውበት እንደሚሰሩ በአፅንኦት ገልፀውልኝ። በተረፈ ” በብሄራዊ ደረጃ የተቋቋመ ኮሚቴ ስላለ እነርሱን መጠየቅ ትችላለህ ” ብለውኛል ። የቀድሞው የኢትዮጵያ የሃገር ፍቅር ማህበር የተቋቋመው የአሁኑ ሃገር ፍቅር ቴአትር ባለበት ቦታ ላይ የተቋቋመ ሲሆንበሁለተኛው የጣሊያን ወረራ ወቅት በወቅቱ በፋሺስት ኢጣሊያን እና ሃገራቸውን በከዱ ባንዳዎች በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ብሎም በኢትዮጵያዊነት ህልውና ላይ በጋራ በተነሱበት ወቅት ለነፍሳቸው በማይሳሱ እና ሃገር ወዳድ በነበሩ ኢትዮጵያውያን የተቋቋመ ማህበር ነበር። ዛሬ በታሪክ ላይ የሚፈፀመው ደባ በታሪካዊው ቴአትር ቤት መሆኑ የበለጠ ልብን ያደማል። ነገ ሁላችንም በታሪክ ፊት መቅረባችን አይቀርም ። የዚያን ጊዜ ምላሻችን ምን እንደሚሆን እንጃ ። መቼም ” አስገድደውኝ እንጂ አምኜበት አይደለም የሰራሁት” እንደማትሉ እርግጠኛ ነኝ። እንኳን ለ 127ኛው የአድዋ ድል በዓል በሰላም አደረሰን!!! © Yehualashet Zerihun
Source: Link to the Post