በታጣቂዎች ታግተው የነበሩት የዳንጎቴ ሲሚንቶ ሠራተኞች ከፍተኛ ገንዘብ ከፍለው ተለቀቁ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ህዳር 27 ቀን 2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ሸዋ በኦሮሚያ…

በታጣቂዎች ታግተው የነበሩት የዳንጎቴ ሲሚንቶ ሠራተኞች ከፍተኛ ገንዘብ ከፍለው ተለቀቁ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ህዳር 27 ቀን 2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ሸዋ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ውስጥ ባለፈው ሳምንት በታጣቂዎች ታግተው የነበሩት የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ሠራተኞች ከፍተኛ የማስለቀቂያ ገንዘብ ከፍለው ተለቀዋል። ከ30 በላይ የሚሆኑት የፋብሪካው ሠራተኞች ምዕራብ ሸዋ ዞን አደአ በርጋ ወረዳ ውስጥ ረቡዕ ኅዳር 21/2015 ዓ.ም. ንጋት ላይ ነበር በታጣቂዎች ታግተው የተወሰዱት። ምንጮች እንዳሉት በሠራተኞቹ ላይ እገታውን የፈጸመው መንግሥት በሽብርተኝነት የፈረጀው እና ‘ሸኔ’ ብሎ የሚጠራው፣ በአካባቢው እንደሚንቀሳቀስ የሚነገረው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂ ቡድን አባላት ናቸው። የታጣቂ ቡድኑ አባላት ካገቷቸው በፋብሪካው አውቶብስ ተሳፍረው ሲጓዙ ከነበሩት ሠራተኞች መካከል የሥራ ድርሻቸው ጽዳት እና ጥበቃ የሆኑትን በመለየት ከለቀቁ በኋላ 17 ሰዎችን ይዞ አቆይቶ ነበር። የሠራተኞች እገታ ባጋጠመ ወቅት የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ሁለት ኃላፊዎች 17 ያህል ሠራተኞች የት እንዳሉ እንደማያውቁ ተናግረው ነበር። በታጣቂዎቹ ታግተው ለቀናት የቆዩት ሠራተኞች ከ300 ሺህ እስከ 500 ሺህ ብር የማስለቀቂያ ገንዘብ ከፍለው ባለፈው ቅዳሜ እና ዕሁድ ተለቀዋል። ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ ነዋሪ እና የፋብሪካው ኃላፊዎች ሠራተኞቹ የሲሚንቶ ግብዓት ተቆፍሮ ወደሚወጣበት ስፍራ በድርጅቱ የሠራተኞች ማመላለሽ አውቶብስ እየተጓዙ ሳለ ነበር በታጣቂ ቡድኑ አባላት የታገቱት። ይህ ሠራተኞቹ በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አባላት የታገቱበት ፋብሪካ የሚገኘው ከአዲስ አበባ በስተ ምዕራብ አቅጣጫ 90 ኪሎ ሜትር ያህል ርቆ ነው። እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራው ቡድን በስፋት በሚንቀሳቀስበት በዚህ አካባቢ ከፍተኛ የደኅንነት ስጋት ያለ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደምም በዚህ አካባቢ ሰዎችን አግቶ ገንዘብ መጠየቅ በተደጋጋሚ እየተከሰተ ያለ ጉዳይ መሆኑን ነዋሪዎች ተናገረዋል። በቢቢሲ ይህንና ተመሳሳይ የእገታ ድርጊቶችን በተመለከተ ከአካባቢው እና ከክልሉ ኃላፊዎች ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም። ዘገባው የቢቢሲ አማርኛ ነው።

Source: Link to the Post

Leave a Reply