በትናንትናው እለት በተከሰተው የእሳት አደጋ ከ3 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ንብረት መውደሙን የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

በበዓል መዳረሻም ሆነ በእለቱ ድንገተኛ የእሳት አደጋ እንዳያጋጥም የቅድመ ጥንቃቄ መልክቶችን በማስተላለፍና ምላሽም ለመስጠት ዝግጅት ያደረገ ቢሆንም ሁለት የእሳት አደጋዎች መከሰታቸውን ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡በአዲስ አበባ የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮምሽን የህዝብ ግንኙነት ቡድን መሪ አቶ ጉልላት ጌታነህ ለአሀዱ እንደተናገሩት  ታህሳስ 29 ቀን  በቂርቆስ ክፍለከተማ  ወረዳ 9 ልዩ ስሙ መሷለኪያ ወይም ቄስ ሰፈር በሚበል አካባቢ መንስኤው ባልታወቀ ምክንያት በተነሳ የእሳት አደጋ  የመኖሪያ ቤትና ሱቆች ላይ ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል፡፡

በደረሰው የእሳት አደጋ ከ3 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ንብረት መውደሙንና  ከ30 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ንብረትን ማዳን መቻሉን የገለጹት አቶ ጉልላት፤ እሳቱን ለማጥፋት 2 ሰዓት የፈጀ ስራ የተሰራ ሲሆን 24 ተሸከርካሪዎችን በመጠቀም 109 ሰራተኞን በማሳተፍ እንዲሁም 145 ሺህ ሊትር ውሀ መጠቀማቸውን ተናግረዋል፡፡በተመሳሳይም ታህሳስ 29 ቀን በቦሌ ክፍለከተማ ወረዳ 12 ልዩ ስሙ 93 ቁጥር ማዞሪያ በመባል በሚታወቀው አካባቢ በመኖሪያ ቤት ውስጥ በተለኮሰ ሻማ በተነሳው የእሳት አደጋ  ከ50ሺ ብር በላይ የሚገመት ንብረት ሲወድም ሁለት ሚሊየን ብር የሚገመተውን ማዳን መቻሉን ገልጸዋል፡፡እሳቱን ለማጥፋት 15 ሰራተኞች የተሳተፉ ሲሆን ከ6ሺ ሌትር በላይ ውሀ ጥቅም ላይ ውሏል፡፡

እንዲሁም በኮልፌ ቀራኒዮ በተመሳሳይ ቀን ወረዳ አምስት አካበቢ በቆሻሻ ማቃጠል ምክንያት   የእሳት አደጋ የተነሳ ቢሆንም ምንም ኪሳራ ሳያጋጥም ጉዳት ሊደርስበት የሚችል 1 ሚሊየን ብር  የሚገመት ንብረት ማትረፍ እንደተቻለም አቶ ጉልላት ተናግረዋል፡፡በሁሉም ቦታዎች በደረሱት የእሳት አደጋዎች በሰዎች ህይወት ላይ ምንም አይነት ጉዳት አለመድረሱ ተገልጻል፡፡

**********************************************************

ቀን 30/04/2013

አሀዱ ራዲዮ 94.3

Source: Link to the Post

Leave a Reply