በትግራይ በድርቅ ምክንያት አብዛኛው ማህበረሰብ ከፍተኛ ጉዳት እንዳጋጠመው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግኑኝኘት እና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አረጋገጠ፡፡

በትግራይ ክልል የተከሰተው ድርቅ በተመለከተ በክልሉ ጉብኝት ያደረገው ምክር ቤቱ በክልሉ የተከሰተው ድርቅ ውስብስብ በመሆኑ የሁሉም ድጋፍ ያሻዋል ብሏል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት የፌደራሉ እና የክልሉ መንግስት በመናበብ ለኢትዮጵያዊያን፣ ለዓለም አገራትና ለዓለም አቀፍ ድርጅቶች ችግሩን በልኩ ማሳወቅ አለባቸው ብለዋል።

ክልሉን ወደ ነበረበት ለመመለስና የተከሰተውን የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ቀውስ በአስቸኳይ ለመቀልበስ ርብርብ እንደሚያስፈልግ ያመላከተው ቋሚ ኮሚቴው፤ ለእናቶች፣ ለአረጋዊያን እና ለህፃናት ልዩ ድጋፍ እንደሚያስፈልግም አስገንዝቧል።

የምክር ቤቱ የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጎዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶ/ር ዲማ ነጎ በድርቅ ምክንያት አብዛኛው የክልሉ ማህበረሰብ ከፍተኛ ጉዳት አጋጥሞታል ሲሉ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ዶ/ር ዲማ ችግሩ በጣም ውስብስብ እንደሆነና የተቀናጀ ሥራ እንደሚያስፈልግ እንዲሁም የተለያዩ አካላት ሊሳተፉበት እንደሚገባ አስረድተው፣ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ማንኛውም ማህበረሰብ ምግብ አጥቶ መሞት የለበትም ብለዋል።

የክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የክትትልና ግምገማ ባለሙያ አቶ ፍስሃ ባራኪ የተፈጥሮ ድርቅ ለክልሉ ስጋት እንደሆነ አስረድተው፣ 36 ወረዳዎች በድርቅ እንደተጎዱ በተለይ በ8 ቀበሌዎች ውስጥ 1.5 ሚሊዮን ህዝብ መጎዳቱን አስረድተዋል።

በክልሉ መዘራት ከነበረበት 1.3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት 49 በመቶ ብቻ እንደታረሰ አቶ ፍስሃ ለቋሚ ኮሚቴው አብራርተዋል።

በጦርነቱ ምክንያት 335 የጤና ተቋማት እንደወደሙና ማህበረሰቡም ወባ፣ ታይፈስ፣ ራቢስና ሌሎች በሽታዎች እየተባባሱ በመምጣታቸው እና በምግብ እጥረት ምክንያት በሽታዎችን መቋቋም አልቻለም ብለዋል።

ባለሙያው አክለውም 105 ትምህርት ቤቶች ተፈናቃዮች እንደተጠለሉባቸውና 522 የሚሆኑት ደግሞ በተለያዩ ሀይሎች ሥር መሆናቸውን አቶ ፍስሃ አብራርተው ለቋሚ ኮሚቴው አብራርተዋል።

የካቲት 05 ቀን 2016 ዓ.ም

Facebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Source: Link to the Post

Leave a Reply