በትግራይ ክልል በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚደርሰውን ጾታዊ ጥቃት መከላከልን መሰረት ያደረጉ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ገልጿል፡፡

በክልሉ ከህግ ማስከበር ዘመቻወም በፊት በተለይ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወደ ኢትዮጵያ በገባበት ወቅት በአንድ ወር ውስጥ ከ40 በላይ ሴቶች እና ህፃናት ላይ ጾታዊ ጥቃት መድረሱን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ገልጿል፡፡

ሴቶችና ህጻናት ላይ ስለሚፈፀሙ ጥቃቶች ምላሽ ከመስጠት ባሻገር መከላከልን መሰረት ያደረጉ ስራዎች መስራት እንዳለባቸው የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች  ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሙና አህመድ ለአሀዱ ተናግረዋል፡፡

በዚህም ረገድ ጾታዊ ጥቃቱን ለመከላከል እና ምላሽ ለመስጠት ከጤና ሚኒስቴር፣ ከጠቅላይ አቃቤ ህግ፣ ከመከላከያ ሰራዊት እና ከፖሊስ የተውጣጣ ግብረ ሃይል በድጋሚ ወደ ስራ መግባቱን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ ሴቶች የደረሰባቸውን የስነ-ልቦና ጉዳት የሚያክሙ ባለሙያዎችም ስልጠና እየተሰጣቸው መሆኑን አብራርተዋል፡፡

አያይዘውም በክልሉ አይደር ሆስፒታል ብቻ አገልግሎቱን እየሰጠ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታዋ ገልጸው ከጤና ሚኒሰቴር ጋር በጋራ በመሆን በቀጣይ የማስፋፋት ስራ እንደሚሰራ አስረድተዋል፡፡

የሴቶችና ህጻናት ጥቃት የሰብዓዊ መብት ጥሰት በመሆኑ ጥቃት አድራሾች በወንጀል ሊጠየቁ እንደሚገባ ሚኒስትር ዴኤታዋ ወይዘሮ ሙና አህመድ ጠቁመዋል፡፡

ቀን 22/06/2013

አሐዱ ራዲዮ 94.3

Source: Link to the Post

Leave a Reply