በትግራይ ክልል በድርቅ ሳቢያ ቢያንስ 351 ሰዎች መሞታቸው እርግጥ ሆኗል ተባለ

የኢትዮጵያ የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በዛሬው እለት ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው ተቋሙ በተመለከታቸው ሁለት የትግራይ ክልል ዞኖች ውስጥ ብቻ በድርቅ ሳቢያ 351 ሰዎች መሞታቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል።

በትግራይ እና አማራ ክልሎች ያለውን የድርቅ ሁኔታ በተመለከተ የወጣው መግለጫን አዲስ ማለዳ የተመለከተች ሲሆን በዚህም በትግራይ ክልል ማዕከላዊ ዞን እና ደቡብ ምስራቅ ዞን ክትትል መደረጉ ተገልጿል። በሁለቱ ዞንች ውስጥ ከሚገኙ ሁለት ወረዳዎች ብቻ በድርቅ ሳቢያ ከ15 ሺህ በላይ ዜጎች ተፈናቅለዋል።

በተመሳሳይ በድርቁ ሳቢያ በማዕከላዊ ዞን 334 ሰዎች ሲሞቱ 91 ሟቾች ከአበርገለ ወረዳ መሆናቸውን ያመለከተው መግለጫ፤ በደቡብ ምስራቅ ዞን ‘ኢስራ ወአዲ ወጅራት’ ወረዳ ሌሎች 17 ሰዎች ሲሞቱ የኢትዮጵያ የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በድምሩ 351 ሰዎች መሞታቸውን “ማረጋገጥ” ተችሏል ብሏል። በእነዚሁ ወረዳዎች ውስጥ ከ46 ሺህ በላይ እንስሳት ሲፈናቀሉ 298 የሚሆኑ እንስሳት ሞተዋል።በትግራይ ክልል በሚገኙትና ተቋሙ ክትትል አደረግኩ ባለባቸው ወረዳዎች ውስጥ ከ3 ሺህ 700 የሚበልጡ ተማሪዎች በድርቁ ምክንያት ትምህርት አቋርጠዋል። አዲስ ማለዳ ከመግለጫው እንደተመለከተችው “በኢስራ ወአዲ ወጅራት ወረዳ 1069፤ በጭላ አበርገሌ ወረዳ ደግሞ 2659 በድምሩ 3728 የሚሆኑ ተማሪዎች በድርቁ ምክንያት የሚበሉትና የትምህርት ቁሳቁስ በማጣት ማቋረጥቻውን ለማወቅ ተችሏል”።

መግለጫው የተመለከተው ሌላኛ የአማራ ክልል የድርቅ ሁኔታ ሲሆን የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋሙ እንዳለው የክልሉ መንግስት ረሃብ አልተከሰተም የሚል ሪፖርት ቢሰጥም “መረጃ በሰበሰብንባቸው ወረዳዎች ግን የተከሰተው ድርቅ ወደ ረሃብ የተሸጋገረ እና በዜጎች ጤና እና ህይወት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማስከተሉ” ተረጋግጧል ሲል አስታውቋል።

በተጨማሪም የአማራ ክልል የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማስተባበሪያ ኮሚሽን በድርቅ የሞተ ሰው የለም ቢልም በሰሜን ጎንደር ዞን እና በዋግኽምራ ዞን 21 ሰዎች ድርቁ ባስከተለው ረሃብ ሲሞቱ 23 ህጻናት ተገቢውን እድገት ባለማግኘታቸው ህይወታቸው አልፎ ተወልደዋል ሲል ተቋሙ አስታውቋል። 

በአማራ ክልል የድርቁ ሁኔታ በእንስሳት ላይ የፈጠረውን ተጽዕኖ በተመለከተ አዲስ ማለዳ የተመከተችው መግለጫ፤ ቢያንስ ከ77 ሺህ 500 በላይ እንስሳት ሲሞቱ ከ201 ሺህ የሚልቁት እንዲሰደዱ አድርጓል። የአማራ ክልል መንግስት ለድርቅ ተፈናቃዮች “የመጠለያ ጣቢያ የሚባል አያስፈልግም” የሚል አቅጣጫ ተሰጥቷል ያለው የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋሙ ይህም የድርቅ ተጋላጭ ዜጎችን መብት የሚጥስ እና ዓለም አቀፍ እርዳታ ለማስተባበር እንቅፋት ሆኗል ተብሏል።

እንደተቋሙ መረጃ ከሆነ ከአንድ ሚልየን የሚልቁ ሰዎች በአማራ ክልል ለንጹህ ውሃ ችግር የተዳረጉ ሲሆን በሺዎፕች የሚቆጠሩ ሰዎች ለወባ እና ኮሌራ በሽታዎች ተጋላጭ ናቸው ተብሏል።

የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በፌደራል የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን እና በክልሎች መካከል የተረጂዎች ቁጥር ልየታ ላይ ያለመናበብ ችግር መኖሩን የጠቆመ ሲሆን ለምሳሌም የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በክልሉ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ጨምሮ 4.2 ሚልየን ዜጎች ድጋፍ ይፈልጋሉ ቢልም የፌደራል መንግስቱ ተቋም 2.2 ሚልየን ናቸው ማለቱን አመልክቷል።

በተጨማሪም የድጋፍ ተደራሽነት ክትትል ላይ ያለው ክፍተት በዓለም አቀፍ የረድኤት ተቋማት ዘንድ አመኔታ ማሳጣቱ የተገለጸ ሲሆን የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስራዎች መዳከም እንዲሁም የእርዳታ ማዕከላት ከተረጂዎች ሩቅ መሆናቸው ዋነኛ ክፍተት ሆኖ ተነስቷል።  

Source: Link to the Post

Leave a Reply