በትግራይ ክልል ከእንስሳ ወደ ሰዎች ተላልፏል በተባለ በሽታ የአራት ሰዎች ህይወት ማለፉን ሰምተናል፡፡

በትግራይ ክልል ደቡብ ምስራቅ አከባቢ በቅርጫ ስጋ ምክንያት ከእንስሳ ወደ ሰዎች በተላለፈ እና ‹‹አባ ሰንጋ›› ሊሆን ይችላል በተባለ በሽታ የአራት ሰዎች ህይወት ማለፉን በክልሉ ጤና ቢሮ የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች አስተባባሪ የሆኑት አቶ መብርሃቶም ሀፍቱ ነግረውናል።

ስጋዉን በቅርጫ ወደ 30 የሚሆኑ አባወራዎች ተከፋፍለዉታል ያሉን ሲሆን በቁጥር ደረጃ ግን ከ5መቶ በላይ ሰዎች ስጋዉን መመገባቸዉን ጤና ቢሮዉ ማረጋገጡን ገልጸዋል፡፡

የእነዚህ 4 ሰዎች ህይወት ያለፈዉ በማህበረሰቡ ዉስጥ፣ ሆስፒታል ከደረሱ በኋላ እና በአይደር ሆስፒታል መሆኑን ገልጸዉ ወደ አሁንም ማህበረሰቡ ዉስጥ ሌሎች ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ ነዉ ያሉት፡፡

እስካሁን ለማወቅ እንደተቻለዉ ከሆነ 17 ሰዎች በበሽታዉ የተያዙ ሲሆን ከዛ መሃል ደግሞ አራቱ ህይወታቸዉ ማለፉን ነዉ የነገሩን፡፡

ስለ ችግሩ የሰማነዉ ቅዳሜ ነዉ ያሉት አስተባባሪዉ ሞቶቹ የተከሰቱት ዓርብ ዕለት ነዉ ብለዋል፡፡

የትግራይ ክልል ጤና ቢሮ ጉዳዩን በስፋት እንዲያጣሩ ወደ ቦታዉ የተለያዩ ባለሙያዎችን ዛሬ ጠዋት መላኩን አንስተዉ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች የሚናፈሰዉ ወሬም ትክክል አይደለም ፤ በስፋትም ማጣራት እያደረግንበት እንገኛለን ሲሉ ነግረዉናል፡፡

በተለምዶ ‹‹አባ ሰንጋ›› ወይንም አንትራክስ በመባል የሚታወቀዉ ይህ በሽታ በትግራይም ሆነ በአማራ ክልል ዛሬም ድረስ ያለ በሽታ መሆኑን አቶ መብርሃቶም አንስተዋል፡፡

ጣቢያችን በዚህ ጉዳይ ላይ ሌሎች ተጨማሪ መረጃዎች ሲኖሩ የሚያጋራችሁ ይሆናል፡፡

በእስከዳር ግርማ

ሰኔ 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Facebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Source: Link to the Post

Leave a Reply