በትግራይ ክልል ከ21 ሺህ ሄክታር በላይ በአንበጣ መንጋ መሸፈኑ እንዳሳሰበው የክልሉ የግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡

በትግራይ ክልል በተከሰተው አዲስ የዛፍ ላይ አንበጣ ከ21ሺ ሄክታር በላይ የሚሆን አካባቢን መሸፈናቸውን ቢሮው ለኢትዮ ኤፍ ኤም አስታውቋል፡፡

አሁን የተከሰተው የአንበጣ መንጋ ከዚህ በፊት በክልሉ ታይቶ የማይታወቅ ዓይነት ያሉት የትግራይ ክልል ግብርና እና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ የተባዮች መከላከል ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ መብርሃቶም ገብረኪዳን በተለይም በሽራሮና አካባቢው ከፍተኛ የሆነ የአንበጣ መንጋ መከሰቱን ነግረውናል፡፡

ይህ የአንበጣ መንጋ በተወሰነ መልኩም በሰብል ላይ የተከሰተ ቢሆንም ይህ ነው የሚባል ግን የሰብል ጉዳት አለማደረሱን አቶ መብራህቶም ተናግረዋል፡፡
በክልሉ በተከሰተው የአንበጣ መንጋ ከ21 ሺ ሄክታሩ 13ሺ የሚሆኑት በሽራሮ አከባቢ ያሉ ወረዳዎች ላይ እንደተከሰቱ አንስተዋል፡፡

የተከሰተው የዛፍ ላይ አንበጣ መንጋ ለመከላከል በኬሚካል ርጭት እና በሰው ሃይል በመጨፍጨፍ ከ60 በመቶ በላይ የሚሆነውን መቀነስ መቻሉን ለጣብያችን ተናግረዋል፡፡

የአንበጣ መንጋውን ለማጥፋት ከፍተኛ የሆነ ርብርብ እየተደረገ እንደሆነ በመግለፅ ነገር ግን በበጀት እጥረት በከፍተኛ ሁኔታ እንደተቸገሩ ገልፀዋል፡፡
በትግራይ ክልል ከአንበጣ መንጋው በተጨማሪ በደቡብ ምስራቅ እና ደቡባዊ ዞኖች ድርቅ መከሰቱን መገለፁ አይዘነጋም፡፡

በአቤል ደጀኔ

መስከረም 24 ቀን 2016 ዓ.ም

Facebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Source: Link to the Post

Leave a Reply