በትግራይ የመልሶ ማቋቋም እና የመልሶ ግንባታ ጥረቶች ፍጥነት መጨመር አለባቸው ሲል ኢሰመኮ ገለጸ፡፡የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በትግራይ ክልል ያለዉን የሰብዓዊ መብት እንዲሁም የሰብዓ…

በትግራይ የመልሶ ማቋቋም እና የመልሶ ግንባታ ጥረቶች ፍጥነት መጨመር አለባቸው ሲል ኢሰመኮ ገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በትግራይ ክልል ያለዉን የሰብዓዊ መብት እንዲሁም የሰብዓዊ ሁኔታ በተመለከተ ያሰባሰበዉን የክትትል ሪፖርት ይፋ አድርጓል፡፡

ኮሚሽኑ በክልሉ በሚገኙ ማዕከላዊ፣ ሰሜን ምዕራብ፣ ደቡባዊ፣ ደቡብ ምስራቅ እና በመቀሌ ልዩ ዞን ያደረገዉን የክትትል ሪፖርት ነዉ ይፋ ያደረገዉ፡፡

ኮሚሽኑ አላማዉ አድርጎ የተነሳዉ ጉዳይ በክልሉ ያለዉን የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ነዉ ተብሏል፡፡

በክልሉ ያለዉን የሰብዓዊ ሁኔታ ፤ የአገር ዉስጥ ተፈናቃዮች ትምህርት የማግኘት መብት፣ የጤና አገልግሎት የማግኘት መብት፣ ከግጭት ጋር የተያያዙ ጾታዊ ጥቃቶችን፣ የእስረኞችን መብት እና የህግ አፈጻጸም፣ ከህግ ዉጪ የሚፈጸሙ ግድያዎች፣ አላግባብ አያያዝ፣ ጠለፋዎች ፣በግዳጅ መሰወር እንዲሁም በግዳጅ ማፈናቀል ላይ ትኩረቱን ያደረገ መሆኑን ገልጿል፡፡

በክልሉ ያለዉ ሰብዓዊ ሁኔታ በተለይ ደግሞ ለአገር ዉስጥ ተፈናቃዮች የሚደርሰዉ የምግብ እና ሌሎች መሰረታዊ ድጋፎች በፍጹም በቂ አለመሆኑን አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡

በዚህ ችግር ላይ ደግሞ ከዚህ በፊት የእህል ድጋፍ የሚያደርጉ አጋር አካላት ድጋፉን ማቋረጣቸዉ ሁኔታዉን የከፋ እንዳደረገዉ አስታዉቋል፡፡

ኮሚሽኑ በሰዓቱ ምልከታ አደረግኩባቸዉ ባላቸዉ መጠለያ ጣቢያዎች የነበረዉ የምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ እንደ ድንኳን እና የጤና አገልግሎቶች ያሉ መሰረታዊ ጉዳዮች የሉም ማለት የሚቻልበት ሁኔታ ላይ ናቸዉ ማለት እንደሚቻል ነዉ ያነሳዉ፡፡

በክልሉ አንዳንድ ቦታዎች ላይ በጦርነቱ የወደሙ እና የተዘረፉ የጤና እና የትምህርት ተቋማት እንደምንም ስራ የጀመሩበት ሁኔታ ፤ ባለሙያዎችም ወደ ተቋማቱ የተመለሱበት ሁኔታ ቢኖርም አሁንም የመልሶ ማቋቋሙ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብሏል፡፡

አሁንም በክልሉ የጤና እና የትምህርት አገልግሎቶችን ማግኘት አስቸጋሪ ነዉ ያለዉ ኮሚሽኑ፤ ጉብኝት ያደረገባቸዉ ትምህርት ቤቶችም ለአገር ዉስጥ ተፈናቃዮች ማቆያዎች መሆናቸዉን ገልጿል፡፡

በተጨማሪም በቂ የሆነ የትምህርት ቁሳቁሶች አለመኖር እንዲሁም ከትምህርት ያቋረጡ ልጆች መብዛት የትምህርት አገልግሎቱ በበቂ እና በተሟላ ሁኔታ እንዳይቀጥል ፈተና ሆኖበታል ነዉ ያለዉ፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ምልከታ ባደረገበት የቆላ ተምቤን ወረዳ የአቢ አዲህ ከተማ እና የጉያ ቀበሌ ትምህርት ቤቶች ዉስጥ ያለዉ የአይሲቲ ቁሶች፣ ላይብረሪዎች፣ ላብራቶሪዎች እንዲሁም የቢሮ መገልገያ ዕቃዎች አብዛኛዉ የተዘረፉ ሲሆን ቀሪዎቹ ደግሞ መቀየር አልያም መጠገን የሚያስፈልጋቸዉ ናቸዉ ብሏል፡፡

በደቡባዊ ትግራይ ዞን ብቻ ከጦርነቱ በፊት ከ2መቶ30 ሺህ በላይ ተማሪዎች የነበሩ ሲሆን ፤ኢሰመኮ ክትትል ባደረገበት ወቅት ከጦርነቱ በኋላ ወደ ትምህርት የተመለሱት 70ሺህዎቹ ብቻ ናቸዉ ብሏል፡፡

በዞኑ ከነበሩት 7ሺህ 3መቶ51 መምህራን ደግሞ ወደ ስራ የተመለሱት 3ሺህ 1መቶ 52 የሚሆኑት ብቻ መሆናቸዉን ገልጿል፡፡
እስከዳር ግርማ

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን

የካቲት 12 ቀን 2016 ዓ.ም

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ወቅታዊ አዳዲስ መረጃዎችና ፕሮግራሞችን ለማግኘት ከታች ያሉትን ገፆቻንን ይጎብኙ ቤተሰብ ይሁኑ ።

Telegram https://t.me/ethiofm107dot8

Twitter https://twitter.com/EthioFM

YouTube https://www.youtube.com/@onelovebroadcast/videos

Facebook https://www.facebook.com/onelovebroadcast

Source: Link to the Post

Leave a Reply