በትግራይ የተፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በሽግግር ፍትህ ብቻ መታየት አለባቸው ተባለ።

በትግራይ የተፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በሽግግር ፍትህ ብቻ ሊታይ ይገባል ሲል ቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች አስታውቋል።

የትግራይ ግዜያዊ አስተዳደር በሰጠው መግለጫ መሰረት በትግራይ ጦርነት ወቅት ከባድ ወንጀሎች የፈፀሙ 212 ምርኮኞችን የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት ለማፅናት ሲባል በምህረት መልቀቁን መግለፁ ይታወሳል።

ይህንንም ተከትሎ ጣብያችን ኢትዮ ኤፍ ኤም ከቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች ምክትል ዳይሬክተር አቶ መብሪህ ብርሃነ ጋር ባደረገዉ ቆይታ ከባድ አለም አቀፍ ወንጀል በትግራይ ህዝብ ላይ ፈፅመዋል የተባሉ ምርኮኞች ለተፈፀመው ከባድ የመብት ጥሰት ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ጉዳያቸው ከፖለቲካ እሳቤ ውጭ በሚከናወን የሽግግር ፍትሕ መታየት ያለበት መሆን አለበት ብለዋል።

የትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደርም የወንጀሉ ፈፃሚዎች በምህረት ለመልቀቅ የሚያስችል የሕገ-መንግስት ይሁን የፍትሕ መሰረት እንደሌለው ቅድሚያ ለሰብዓዊ መብት በፅኑ እንደሚያምን ገልፀዋል፡፡

በተባበሩት መንግስታት የተቋቋመው የሰብዓዊ መብቶች ባለሙያ ኮሚሽን በትግራይ ጦርነት ውስጥ ከባድና መጠነ ሰፊ የጦር ወንጀሎች፣ በሰብዓዊነት ላይ ወንጀሎች መፈፀማቸዉን በምርመራ መግለፁ ይታወቃል።

ጦርነቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የትግራይ ክልል ሰላማዊ ነዋሪዎችን ለሞት፣ ለአካል ጉዳት፣ ለአስገድዶ መደፈር፣ ለመፈናቀል እና ለሌሎች ሰብአዊ ቀውሶች መዳረጉ መዘንጋት የለበትም ሲሉም ምክትል ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።

ይሁን እንጂ በፌዴራል መንግስት ይሁን የትግራይ ግዜያዊ አስተዳደር እስካሁን ድረስ የወንጀሉን ፈጻሚዎች ለፍትሕ ለማቅረብ ይሁን ተጎጂዎችን ለመርዳት የወሰዱት ተጨባጭ እርምጃዎች የለም ሲሉ ይከሳሉ።

አሁንም የፌዴራል መንግስት እና የትግራይ ግዜያዊ አስተዳደር በትግራይ ክልል ውስጥ ለተፈፀመው አለም አቀፍ ወንጀሎች ያለ ተጠያቂነት ለፖለቲካ ትርፍ ተብሎ ተዳፍኖ እንዳይቀር እና አጥፊዎች በፍትሕ አደባባይ እንዲያቀርቡ ጠይቀዋል።

በተጨማሪም ለተጎጂዎችና ለተጎጂዎች ቤተሰብ ድጋፍ እንዲሰጡ፣ እንዲክሱ እና ዕርቅና ስምምነት እንዲፈጥሩ ቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች ጥሪውን አስተላልፈዋል።

በአቤል ደጀኔ

መጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ.ም

Facebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Source: Link to the Post

Leave a Reply