You are currently viewing በኃይል እርምጃ የሕዝብን ጥያቄ መፍታት አይቻልም! በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከኢሕአፓ፣ መኢአድ፣ ዐማራ ግዮናዊ ንቅናቄ ፣ አንድ ኢትዮጵያ  ዴሞክራሲያዊ  ፓርቲ እና እናት ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ!…

በኃይል እርምጃ የሕዝብን ጥያቄ መፍታት አይቻልም! በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከኢሕአፓ፣ መኢአድ፣ ዐማራ ግዮናዊ ንቅናቄ ፣ አንድ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እና እናት ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ!…

በኃይል እርምጃ የሕዝብን ጥያቄ መፍታት አይቻልም! በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከኢሕአፓ፣ መኢአድ፣ ዐማራ ግዮናዊ ንቅናቄ ፣ አንድ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እና እናት ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ! እልህና ፉክክር የተጠናወተው የአገራችን ፖለቲካ ኃላቀር የሆነውን የጎሳ ፖለቲካ አስተሣሰብ፣ በውሥብሥብ ሤራና ጥልቅ ጥላቻ የተበከለውን እሣቤና በዚያው መንገድ እየቀጠለ ያለውን ችግርና መከራ የበለጠ የማስቀጠል ሂደቱን ተያይዞታል። ብልጽግና መራሹ መንግሥት የግብር ሳይሆን የስም ብቻ ቅያሬ አድርጎ ሥልጣን ከተቆናጠጠበት ጊዜ ጀምሮ የሕዝብን ብሶት ከማድመጥ እና ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ ከመፍታት ይልቅ በእኔ ብቻ አውቅላችኃለሁ የእውር ድንብር ጉዞ ሕዝባችንን ማጥ ውስጥ አገራችንን ደግሞ ከእለት ወደ እለት ወደ ከፋ ቀውስ ውስጥ እየከተታት ይገኛል። እዚህም እዚያም የ…ሚደመጡ ዋይታዎችና የድረሱልን ጥሪዎች በጆሮ ዳባ ልበስ እየታለፉ አንዱ ችግር በሌላው ችግር ላይ እየተደራረበ ነው። መሠረታዊ የሆኑት ችግሮቻችን ሊፈቱ የሚችሉት በጥልቅ ውይይትና ንግግር ብቻ መሆኑን ጠቅሰን ባለፉት ተደጋጋሚ ጊዜያት ያቀረብናቸውን ጥሪዎች ቸል በማለት መንግሥት ከሠሜኑ ደም አፋሣሽ ጦርነት በውል ሣናገግም አሁንም በማን አለብኝነት በአማራ ክልል እያካሄደ ባለው ጦርነት ንጹሐን ዜጎች በግፍ እየተገደሉ ነው። ከነሐሴ ፲፱ – ፳፪ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም ባሉት ቀናት ብቻ የመከላከያ ሠራዊት በደቡብ ጎንደር ዞን የእብናት ከተማ በተከታታይ በሰነዘረው የከባድ መሳሪያ ጥቃት ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ንጹሃን ወገኖቻችን መገደላቸውን ከምንጮቻችን አረጋግጠናል። ከሟቾች ውስጥም ህጻናት፣ አረጋውያን እና ሴቶች እንደሚገኙበት ለመረዳት ችለናል። በጸበል ስፍራ የሚገኙ ንጹሃን ወገኖቻችን ጭምር የጥቃቱ ሰለባ መሆናቸውንም መረጃዎች ያሳያሉ። በተመሳሳይ በአገር ሽምግሌዎች አሸማጋይነት ወደ ደብረ ታቦር ከተማ የገባው የመከላከያ ሠራዊትም ከተማው ላይ ከባድ መሣሪያዎችን በማጥመድ ለተከታታይ ቀናት ያለማቋረጥ በከተማ ውስጥ እና ከከተማ ውጭ ያሉ ቦታዎችን ዒላማ በማድረግ ሲታኮስ እንደሰነበተ ለመረዳት ችለናል። በተኩሱ በንጹሃን ዜጎች ላይ የደረሰውንም ጉዳት በመከታተል ላይ እንገኛለን። በተመሳሳይ በአዲስ ዘመን፣ በወረታ፣ በደብረ ማርቆስ፣ በፍኖተ ሰላም፣ በላሊበላ እና በሌሎቹ የክልሉ አካባቢዎች ላይም ጥቃቱ ተጠናክሮ በመቀጠሉ ንጹሐን ዜጎች በከፍተኛ ስጋት እና መከራ ውስጥ ይገኛሉ። በተጓዳኝ ሕዝባዊ ትግሉን ተከትሎ የአገር መከላከያ ሠራዊትም እየወሰደ ባለው እርምጃ ከባድ ጉዳት እየደረሰበት ነው። ይህም የመከላከያ ሠራዊቱ ዋነኛ ተግባር የሆነውን አገርን ከውጪ ከሚሰነዘር ጥቃት በብቃት የመከላከል ኃላፊነቱን መወጣት ወደማይችልበት ደረጃ ሊያደርሰው ይችላል። በመንግሥት ማንአለብኝነት እየተከናወነ የሚገኘው የወንድማማቾች ጦርነት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ትልቅ ስጋት ውስጥ የሚከት በመሆኑ ፓርቲዎቻችንን በእጅጉ እንደሚያሳስባቸው አጽንኦት ሰጥተን ለመግለጽ እንወዳለን። የአማራ ክልል ዋና ዋና መንገዶች እየተከናወነ በሚገኘው ጦርነት ምክንያት በመዘጋታቸው ለእለት ጉርስ እና ጤና አስፈላጊ የሆኑ ሸቀጦችና የፍጆታ እቃዎች ለህዝባችን እንዳይደርሱ ሆነዋል። በዚህ ምክንያት ጤፍን ጨምሮ ሌሎች መሠረታዊ የምግብ ፍጆታዎች ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ አሳይተዋል። በዚህ መነሻነት ጦርነቱ ከመጀመሩም በፊት የከፋ የኑሮ ሁኔታ እያስተናገደ በሚገኘው ሕዝባችን ላይ ተባብሶ የቀጠለው የኑሮ ቀውስ አስጊና ሰቅጣጭ ደረጃ ላይ ደርሷል። በሌላ አንጻር በቅርቡ በተመሠረቱት የደቡብ ኢትዮጵያ እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ውስጥ የሚገኙ ዜጎቻችን እያነሱ በሚገኙት ራስን በራስ የማስተዳደር፣ የክልልነት ጥያቄዎች፣ የርዕሰ ከተማ መቀመጫ ጥያቄዎች እና መንግሥት እነዚህ ጥያቄዎች አንዳይነሱ እየወሰደ የሚገኘው እርምጃዎች ሌላ የቀውስ አቅጣጫ እየተከፈተ እንደሆነ ለመረዳት አይከብድም። ከዚሁ ጋር በተያያዘ የጋሞ ወጣቶች ያነሱትን ጥያቄ ተከትሎ የመንግሥት ወታደሮች በወሰዱት የኃይል እርምጃ ከአስራ ስምንት በላይ ንጹሃን ዜጎች መገደላቸውን በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን አውታሮች ይፋ ሆኗል። በጉራጌ፣ ከምባታ እና ስልጤ አካባቢዎች ተመሳሳይ ጥያቄዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውንም ያገኘናቸው መረጃዎች ያሳያሉ። ኢሕአፓ፣ መኢአድ፣ ዐማራ ግዮናዊ ንቅናቄ፣ አንዲት ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እና እናት ፓርቲ እነዚህ ችግሮች አገር እንድትከተል ከተደረገው የጎሳ ፖለቲካ የሚመነጩ በመሆናቸው ዘለቄታዊ መፍትሄ ሊበጅላቸው የሚችለው ሕገ መንግሥቱ ላይ መሠረታዊ ክለሳ በማካሄድ ብቻ መሆኑን የሚያምኑ ሲሆን፤ ይህንኑ ማድረግ እስከሚቻል ድረስ ጉዳዩን በሰከነ መልክ ተመልክቶ ለሕዝብ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ጥረት ማድረግ እንደሚገባ እና የኃይል አማራጭ በየትኛውም መንገድ መፍትሄ ሊሆን እንደማይችል ማስገንዘብ ይወዳሉ። በአማራ ክልል የተነሳውን ሕዝባዊ አመጽም ሆነ በደቡብ ኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች የተነሱ ሕዝባዊ ጥያቄዎችን የኅይል አማራጭ ተጠቅሞ ለመፍታት እየተደረገ ያለው ሙከራ አገርን ወደ ከፋ ቀውስ የሚከት እንዲሁም የመንግሥት ሥልጣን የጨበጡትን ደግሞ ከክብር ዝቅ አድርጎ ሊያሰናብት ወደሚችል አቅጣጫ ሊገፋ እንዲሚችል መተንበይ ከባድ አይሆንም። ምክንያቱም ከሕዝብ ጋር ፍጥጫ ውስጥ ገብቶና ውጊያ ገጥሞ ያሸነፈ መንግሥት የለም። ስለሆነም:- ፩. መንግሥት በአማራ ክልል ያሰማራውን የመከላከያ ሰራዊት በአስቸኳይ አስወጥቶ የአገራችን ዳር ድንበር ሊጠብቅ ወደሚችልበት መደበኛ ሥራው እንዲመልስ እና ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ እንደገለጽነው ለአስቸኳይ አገር አድን ውይይት በሩን ክፍት በማድረግ ችግሮች በውይይትና ድርድር ብቻ እንዲፈቱ አጽንኦት ሰጥተን እናሳስባለን። ፪. መንግሥት በክልል ምስረታ ሥም እያከናወነ የሚገኘው የክላስተር ጥርነፋ በቂ ጥናቶች ያልተደረጉበት፣ የተነሱ መሠረታዊ የማህበረሰብ ጥያቄዎችን እና ውሳኔዎችን ያላገናዘበ በመሆኑ በሕገ መንግሥት ማሻሻያ ተገቢው ማስተካከያ እስኪደረግ በጊዜያዊነት ጉዳዩ በድጋሚ እንዲታይ እናሳስባለን። በመጨረሻም አገር በእንደዚህ ዓይነት ቀውስ ውስጥ በገባችበት ጊዜ በጨለማው ላይ ጥቂት ብርሃን በመፈንጠቅ ሰንደቅ ዓላማችን በዓለም መድረክ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብና ነጭ ላብ እያላባቸው ለህዝባችን በመከራ ዘመኑም ቢሆን በአንድነት ቁሞ የመሥራትን ጥቅም ለፈጠራችሁለት ዕንቁ አትሌቶቻችን ያለንን ታላቅ አድናቆትና ክብር እንገልጻለን። በዚህ የሰቆቃ ወቅት ለዋላችሁት ውለታ የኢትዮጵያ አምላክ ብድራታችሁን ይክፈላችሁ እያልን ለመላው የአገራችን ሕዝብ ከነዚህ እንቁዎቻችን አብሮ የመድክምን እና አብሮ በመቆም ማሸነፍን አሣይተዋልና የምስጋና መልእክታችንን ልናስተላልፍ እንወዳለን። እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ! ኢሕአፓ፣ መኢአድ፣ ዐማራ ግዮናዊ ንቅናቄ፣ አንዲት ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እና እናት ፓርቲ ነሐሴ ፳፫ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

Source: Link to the Post

Leave a Reply