በንብረት ላይ የሚጣለውን ታክስ፤ ክልሎች በባለቤትነት እንዲያስተዳድሩ ተወሰነ   

በሃሚድ አወል

የህዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች፤ በንብረት ላይ የሚጣለውን ታክስ ባለቤትነት ለክልሎች የሚያደርገውን ውሳኔ በአብላጫ ድምጽ አጸደቁ። ሁለቱ ምክር ቤቶች ዛሬ ረቡዕ ጥር 3፤ 2015 ባደረጉት ልዩ ስብሰባ ውሳኔውን ያጸደቁት፤ በአራት ተቃውሞ እና በአምስት ድምጸ ተዐቅቦ ነው።

ምክር ቤቶቹ ከንብረት የሚሰበሰበው ታክስ የክልሎች እንዲሆን የወሰኑት፤ “ከተሞች ከንብረት የሚገኘውን ገቢ በሚገባ በመሰብሰብ የመሰረተ ልማት አቅርቦትን ለማሻሻል፤ የማህበራዊ አገልግሎት ተቋማትን ለመገንባት እንዲጠቀሙበት በማድረግ በመላ ሀገሪቱ ባሉ ከተሞች የሚታየውን ችግር ለማቃለል ይችላሉ” በሚል ምክንያት ነው። በዛሬው ስብሰባ ቀርቦ የነበረው ሁለተኛ አማራጭ፤  የፌደራል እና የክልል መንግስታት በጋራ የንብረት ታክስ የመሰብሰብ ስልጣን እንዲኖራቸው እና በፌዴሬሽን ምክር ቤት በሚወሰነው ቀመር መሰረት ገቢውን እንዲከፋፈሉ የሚያደርግ ነው።

አማራጮቹን ለሁለቱ ምክር ቤቶች ያቀረቡት፤ በፌደሬሽን ምክር ቤት የድጎማ በጀት እና የጋራ ገቢዎች ቋሚ ኮሚቴ እንዲሁም በፓርላማው የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ናቸው። የውሳኔ ሃሳቡን ለሁለቱ ምክር ቤቶች አባላት በንባብ ያሰሙት፤ የድጎማ በጀት እና የጋራ ገቢዎች ቋሚ ኮሚቴ ጸሀፊው አቶ ኃይሉ ኢፋ ናቸው።

የሁለቱ ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች “ከንብረት ታክስ የሚገኘው ገቢ ለአካባቢ መስተዳድሮች መሆን ይገባዋል” የሚል ውሳኔ ማሳለፋቸውን አቶ ኃይሉ ለምክር ቤቶቹ አባላት ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ህገ መንግስት የሚያውቀው የፌደራል እና የክልል መንግስታትን ብቻ መሆኑን ያነሱት አቶ ኃይሉ፤ “ ‘የእዚህ ታክስ ስልጣን ለክልል መንግስታት ተሰጥቶ፤ ክልሎቹ ባላቸው ህገ መንግስታዊ ስልጣን ለአካባቢ መስተዳድሮች ቢሰጡ ይሻላል’ የሚለው አማራጭ በሁለቱም ምክር ቤቶች የቋሚ ኮሚቴዎች ተደግፎ ቀርቧል” ሲሉ የውሳኔ ሃሳቡን ጭብጥ አብራርተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር) 

[በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ ይታከልበታል]

The post በንብረት ላይ የሚጣለውን ታክስ፤ ክልሎች በባለቤትነት እንዲያስተዳድሩ ተወሰነ    appeared first on Ethiopia Insider.

Source: Link to the Post

Leave a Reply