በአሁኑ ሰዓት በአገራችን 6 ሚሊየን ህጻናት የቀነጨሩ ናቸዉ ተባለ፡፡

አገራችን ከመቀንጨር ጋር በተያያዘም በየዓመቱ 55.5 ቢሊየን ብር ታጣለች ተብሏል፡፡

በሰቆጣ ቃልኪዳን የፌደራል ፕሮግራም ማስፈጸሚያ ክፍል ፕሮግራም ማኔጀር የሆኑት ዶ/ር ሲሳይ ሲናሞ ከኢትዮ ኤፍ ኤም ጋር በነበራቸዉ ቆይታ፤አገራችን ከጠቅላላ ጂዲፒ 16.5 በመቶ ወይም 55.5 ቢሊየን ብር ከመቀንጨር ጋር በተያያዘ እንደምታጣ ገልጸዋል፡፡

በ2007 ዓ.ም የተጀመረዉ እና ለ15 ዓመታት የሚቆየዉ የሰቆጣ ቃልኪዳን አላማዉ በ2022 ዓ.ም ዕድሜያቸዉ ከ2 ዓመት በታች የሆኑ ህጻናትን ከመቀንጨር ችግር ነጻ ማድረግ መሆኑንም ዶ/ር ሲሳይ ነግረዉናል፡፡

የመጀመሪያዉ 5 ዓመት የሙከራ ምዕራፍ ትግበራ ነበር ያሉት ዶ/ር ሲሳይ፤እስከ 2013 ድረስ በአማራ እና ትግራይ ዉስጥ የሚገኙ 40 ወረዳዎች ላይ መሰራቱን አንስተዋል፡፡

በዚህም እስከ 3 በመቶ መቀንጨርን መቀነስ መቻሉን እና ከ1መቶ9ሺህ በላይ ህጻናትን ከመቀንጨር መታደግ እንደተቻለ ነዉ ያነሱት፡፡

ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በሁሉም ክልሎች እና ሁለቱን ከተማ መስተዳድሮች ጨምሮ 240 ወረዳዎች ላይ እየተተገበረ መሆኑን ነግረዉናል፡፡

ዶ/ር ሲሳይ እንደሚሉት በዚህ የትግበራ ወቅት ወደ 1 ሚሊየን የሚሆኑ ነፍሰጡር እናቶችን እና ወደ 2.2 ሚሊየን የሚሆኑ ዕድሜያቸዉ ከ2 ዓመት በታች የሆኑ ህጻናትን ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነዉ፡፡

በ2015 ዓ.ም ብቻ ወደ 1መቶሺህ የሚሆኑ ልጆችን ከመቀንጨር መከላከል ተችሏል ያሉት ማኔጀሩ፤ካሉት 240 ወረዳዎች ተጨማሪ ወረዳዎችን ወደ ትግበራ ለማስገባት በዝግጅት ላይ መሆናቸዉንም ለጣቢያችን ተናግረዋል፡፡

በእስከዳር ግርማ

ግንቦት 14 ቀን 2016 ዓ.ም

Facebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Source: Link to the Post

Leave a Reply