You are currently viewing “በአማራው ላይ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ፣ በሰሜን እዝ ላይ ወረራ፣ የአፋር ህፃናትና ተፈናቃይ ሴቶችን በጅምላ የፈጀው፣ በሺህ የሚቆጠሩ ሴቶች ላይ አስገድዶ መድፈር የፈፀመው ህወሓት ከፖለቲካ ተ…

“በአማራው ላይ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ፣ በሰሜን እዝ ላይ ወረራ፣ የአፋር ህፃናትና ተፈናቃይ ሴቶችን በጅምላ የፈጀው፣ በሺህ የሚቆጠሩ ሴቶች ላይ አስገድዶ መድፈር የፈፀመው ህወሓት ከፖለቲካ ተ…

“በአማራው ላይ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ፣ በሰሜን እዝ ላይ ወረራ፣ የአፋር ህፃናትና ተፈናቃይ ሴቶችን በጅምላ የፈጀው፣ በሺህ የሚቆጠሩ ሴቶች ላይ አስገድዶ መድፈር የፈፀመው ህወሓት ከፖለቲካ ተሳትፎው በህግ ታግዶ እንዲቀጥል ይደረግ ሲል ዓለም አቀፉ የአማራ ህብረት ጠየቀ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ህዳር 1 ቀን 2015 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ በኢትዮጵያ መንግሥትና በህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) መካከል የተደረሰውን የሰላም ስምምነት አስመልክቶ ከዓለም አቀፍ የአማራ ህብረት የተሰጠው ሙሉ መግለጫ የሚከተለው ነው:_ ደም አፋሳሽና ትውልድን ጨራሽ የሆነው የእርስ በእርስ ጦርነት ቆሞ ሰላምን ለማስፈን ወደ ስምምነት መመጣቱን ዓለም አቀፍ የአማራ ህብረት በአዎንታዊ ሁኔታ ይመለከተዋል። እንደዚሁም ስምምነቱ የኢትዮጵያን ሉአላዊነትና የግዛት አንድነት ማስጠበቅ ላይ ትኩረት ማድረጉ ጥሩ አቅጣጫ ነው ብሎ ያምናል። ነገር ግን በሰላም ስምምነቱ እንዲመጣ የታሰበው ጊዚያዊ እፎይታ ወይንስ ዘላቂ ሰላም የሚል ቁልፍ ጥያቄ እንድንጠይቅ ተገደናል። በእኛ እምነት ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት የአንዱን ክፍል ፍላጎት በማስጠበቅ የሌላውን ፍላጎት መደፍጠጥ ወይም እንደሌለ መቁጠር ሳይሆን የሁሉንም ህዝብ ጥቅምና ፍላጎት ባስጠበቀ መልኩ በሚደረግ ድርድር የተደረሰ ስምምነት ነው። ይህን እምነታችንን መሰረት በማድረግ በደቡብ አፍሪካ በኢትዮጵያ መንግሥትና በህወሓት መካከል የተደረገው የድርድር ሂደትም ሆነ የተደረሰበት ስምምነት በጦርነቱ ቀጥተኛ ሰለባ የነበሩትን የአማራንና የአፋርን ክልሎች በቀጥታ ያላሳተፈና ጥቅምና ፍላጎታቸውን ያላስጠበቀ በመሆኑ የስምምነቱን ተቀባይነት ጥርጣሬ ላይ እንዲወድቅ አድርጎታል። በዚህ መልኩ ስምምነቱ ቢተገበር አንድ ጦርነት አስቁሞ ለሌላ የማያባራ የእርስ በእርስ ጦርነት የሚጋብዝ እንጅ ህዝቡ የሚናፍቀውን ዘላቂ ሰላም ለኢትዮጵያ ፈፅሞ አያመጣም የሚል ስጋት አለን። ስምምነቱ ተቀባይነት አይኖረውም ወይም ዘላቂ ሰላም አያመጣም ስንል የሚከተሉትን ምክንያቶችና ጭብጦች መነሻ አድርገን ነው። 1. ህወሓት በኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ድርጅት ተብሎ ተፈርጆ ባለበት ሁኔታ የኢትዮጵያ መንግሥት ከአሸባሪ ድርጅት ጋር ያደረገው ስምምነት የህጋዊነት ጥያቄ የሚነሳበት በመሆኑ፣ 2. የእብሪተኛው ህወሓት የወረራ ጦርነት ኢላማና ቀጥተኛ ገፈት ቀማሽ በመሆን በሺህ የሚቆጠሩ ዜጎች በዘር ማጥፋት ወንጀል የተጨፈጨፉባቸው፣ የተገደሉባቸውና፣ አካል ጉዳተኛ የሆኑባቸው፣ ሴቶች የተደፈሩባቸው፣ የእምነት ቦታወቻቸው የተደፈሩባቸውና የተቃጠሉባቸው፣ በብዙ ቢሊዮን ብሮች የሚገመት ሃብት ንብረት የወደመባቸው የአማራና የአፋር ክልሎች በመረጧቸው ወኪሎቻቸው አማካይነት በደቡብ አፍሪካው ድርድር ባለመሳተፋቸው፣ 3. የአማራ ማንነትን ለማስከበር መስዋዕትነት የተከፈለባቸው የአማራ ህዝብ አፅመ ርስቶች ወልቃይት ጠገዴ፣ ሁመራና ጠለምት ከጎንደር ራያ አላማጣ፣ ኮረም፣ ወፍላ፣ መሆኒ፣ ዋጃ ከወሎ አሁን ያለው የኢትዮጵያ ህገ መንግሥት ከመፅደቁ 4 አመት በፊት ህወሓት ስልጣኑን ተጠቅሞ በግድ ወደ ትግራይ ጠቅሏቸው ለ29 አመታት ከሞተ በላይ ከአለ ሰው በታች አድርጎ በአፓርታይድ አገዛዝ ሲያሰቃያቸው ሺሀወችን ጨፍጭፎ ከጭፍጨፋው የተረፉትን ማንነታቸውን አሳጥቶ በቋንቋቸው እንዳይማሩ እንዳይናገሩ፣ አምልኮ እንዳይፈፅሙ፣ ደስታቸውንም ሆነ ሀዘናቸውን በአማርኛ እንዳይገልፁ አድርጎ አስጨንቆ ይዟቸው ከቆየ በኋላ ራሱ በለኮሰው ጦርነት አማራው ለነፃነቱ ባደረገው ተጋድሎ ርስቶቹን በደሙ ማስመለሱ እየታወቀ ጥያቄ የሚነሳባቸው ቦታወች በኢትዮጵያ ህገ መንግሥት መሰረት ችግሩ ይፈታል በሚል ስምምነት ላይ መደረሱ ፈፅሞ ተቀባይነት የሌለው መሆኑ ሊሰመርበት የሚገባ መሆኑ፣ በተጨማሪም ይህ ህገ መንግሥት ሲረቀቅም ሆነ ሲፀድቅ አማራውን ያገለለ ስለነበረ ያልተሳተፈበት ህገ መንግሥት ከመሆኑም በሻገር ህገ መንግሥቱ እንዲለወጥ ጥያቄ ካነሳ አመታት አልፈዋል በዚህም የተነሳ አማራውን አግልሎ በተቀረፀ ህገ መንግሥት ሊዳኝበት የማይገባ በመሆኑ፣ 4. ወራሪው ህወሓት የሰሜን እዝን በአሰቃቂ ሁኔታ በመጨፍጨፍ፣ ጦርነቱን ከጀመረበት ቅፅበት አንስቶ ለሦስት ጊዜ ያህል የአማራውንና የአፋር ክልሎችን በመውረር በማይካድራ፣ በጪና፣ በቆቦ እና አላማጣ በሺ የሚቆጠሩ አማሮች ላይ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ (genocide) የፈፀመ፣ በአፋር ውስጥ ገለምሶ በተባለ ቦታ ተፈናቃዮች ያሉበትን መጠለያ ሆን ብሎ የመድፍ ኢላማ በማድረግ በመቶዎች የሚቆጠሩ ህፃናት ሴቶችና አረጋውያንን የፈጀ፣ እንዲሁም በጦርነቱ ያልተሳተፉ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎችን የገደለ፣ አካል ያጎደለ፣ ሚሊዮኖችን ከቀያቸው ያፈናቀለ፣ የመንግሥት ንብረቶችንም ሆነ የግል አንጡራ ሁብትን አንዳች ሳያስቀር በገፍ የዘረፈ፣ የእምነት ቤቶችን ያረከሰ፣ መሰረት ልማቶችን ያወደመ አሸባሪ ድርጅት ሲሆን ለፈፀመው ወንጀል ሁሉ በህግ ተጠያቂ መሆን ሲገባው ከወንጀሉ ነፃ ሊያደርግ የሚችል ስምምነት መደረሱ፣ 5.በኢትዮጵያ መከላከያና ጠላቴ በሚለው በአማራና አፋር ክልሎች ተደጋጋሚ ወረራ በመፈፀም የአገርን ሉአላዊነት አደጋ ላይ በመጣል ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር አብሮ አገርንና ህዝብን ያደማ እና የከዳ ድርጅት በአገር ክህደት ወንጀል መጠየቅ ሲገባው ወደ ፖለቲካ ህይወት አንዲመለስና በትግራይ ክልል በሚቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲሳተፍ የሚያስችል ስምምነት መደረሱ ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ፣ 6. ህወሓት በአማራና አፋር ክልሎች ባደረጋቸው ተደጋጋሚ ወረራወች በእቅድ የዘረፈውን መጠነ ሰፊ ሀብትና ንብረት እንዲመልስ እንዲሁም ለተጎዱት የካሳ ክፍያ እንዲፈፅም የሚያስችል ራሱን የቻለ ግልፅ የሆነ አንቀፅ የስምምነቱ አካል መሆን ሲገባው ባለመካተቱ፣ 7. በጦር ሜዳ ሙሉ በሙሉ የተሸነፈን ቡድን ሽንፈቱን ተቀብሎ እጅ እንዲሰጥና ሰራዊቱ ተገዶ ትጥቅ እንዲፈታ፣ የጦርና የፖለቲካ አመራሩ እንዲሁም ወንጀል የፈፀሙ ሁሉ ተለይተው ህግ ፊት እንዲቀርቡ ማድረግ እና ህወሓትን ከትግራይና መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጫንቃ ማውረድ ሲገባ ከሞት አፋፍ አድኖ ወደ ድርድር በመውሰድ ነፍስ እንዲዘራ መደረጉ ስህተት ብቻ ሳይሆን የህወሓት በትግራይ ክልል የመሪነት ቦታ መቀጠል ለአማራው፣ ለትግራይ ህዝብ ብሎም ለኢትዮጵያ ዋነኛ የህልውና ስጋት በመሆኑ፣ 8. ከጥንተ ድርጅታዊ ባህሪውና የቅርብ ጊዜ ድርጊቶቹ በመነሳት ህወሓት እንደለመደው ተራራውንና ዋሻውን የመሳሪያ መደበቂያ ያደርገዋል እንጅ በምንም አይነት ያለውን ትጥቅ ይፈታል የሚለው ፈፅሞ ሊታመን የማይችልና ትጥቅ ማስፈታቱን የህወሓት ከፍተኛ የጦር መሪወች ይሳተፉበታል መባሉ ተፈፃሚነቱን ጨርሶ ቀልድ የሚያደርገው መሆኑን በፅኑ ስለምናምን ነው። በመግቢያችን አንደገለፅነው የአርስ በርሱ ጦርነት ቆሞ አስተማማኝና ዘላቂ ሰላም ቢመጣ ዓለም አቀፍ የአማራ ህብረት በአጅጉ የሚሻው ጉዳይ ነው። ሆኖም ግን ችግሩ በጦርነቱ ቀጥተኛ ተጎጂወች የሆኑትን ሁሉንም ሳያሳትፍ በተናጠል በወራሪው ህወሓትና በመንግሥት ብቻ የተደረሰው ስምምነት ዘላቂ ሰላም ሳይሆን ወደማያባራ ጦርነት ያስገባናል ብሎ ድርጅታችን ያምናል። ስለዚህም ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ የኢትዮጵያ መንግሥት ነገሮችን እንደገና ማጤን አለበት እንላለን። የኢትዮጵያ መንግሥት መጨነቅ ያለበት ስለ ጊዜያዊ ስልጣን ማደላደል ሳይሆን ዘላቂና እውነተኛ እርቀ ሰላም እንዲወርድና ህዝቡ ውድ አገሩን ለማልማት በትብብርና በአንድነት እንዲረባረብ አድሎአዊነት የሌለበት ፍትሃዊ እና ቅን አመራር መስጠት ነው፡፡ ይህን እምነታችንን መሰረት አድርገን በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ የሚከተሉትን ጥያቄዎች እናቀርባለን፦ ለኢትዮጵያ መንግሥት:_ 1. ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ህወሓት በጉልበት ከአማራው ወሰዷቸው የነበሩትን በጥቅሉ ወልቃይት እና ራያ የማንነታቸው መሰረት ወደ ሆነው የአማራ ክልል በከፍተኛ መስዋዕትነት ስለተመለሱ የእነዚህን መሬቶች ተጨባጭ ሁኔታ በማጤን፣ ህወሓት ለብዙ አስርተ ዓመታት ያደረሰባቸውን እጅግ ዘግናኝ የሆነ ግፍ በማስታወስ፣ ብሎም ያለ ህዝቡ ፈቃድ ህገ መንግሥቱ ከመረቀቁ በፊት ከጎንደርና ከወሎ ተነጥቀው ወደ ትግራይ ተወስደው የነበሩ በመሆኑ በስምምነቱ አንቀፅ 10 መጨረሻ ላይ እንደተጠቀሰው በህገ መንግሥቱ ይፈታል የሚለው ተለውጦ ወደ አማራ ክልል መመለሳቸውንና የክልሉም አካል መሆናቸውን በአስቸኳይ ህጋዊ እውቅና እንዲሰጣቸውና የበጀት ድልድሉም አካል እንዲሆኑ አጥብቀን እንጠይቃለን። ይህ ባይሆንና በህገ መንግሥቱ ይፈታል በሚል ያለ ህዝብ ፍላጎት በግድ ወደ ትግራይ እንዲካተቱ ቢሞከር ወይንም በፌደራል ስር ይተዳደራሉ የሚል አማራጭ ቢወሰድ ሰላም ሳይሆን የሚመጣው አንዱን ጦርነት አቁሞ ለሌላ የከፋ ጦርነት ማዘጋጀት ስለሚሆን ይህ እንዳይደረግ በጥንቃቄ እንዲታሰብበት ለማስጠንቀቅ እንወዳለን። እዚህ ላይ በመንግሥት ላይ ያለንን አንድ ትዝብት እናንሳ፣ ለመሆኑ በጦርነት ሽንፈት ሲደርስ አማራውን ለሞት መጥራት የእርሱን ወሳኝ እገዛ አግኝቶ በጦር ሜዳ ድል ሲገኝ የአማራውን ጥያቄዎችና ፍላጎቶች ደፍጥጦ በኢትዮጵያ ውስጥ እውነተኛ ሰላም አመጣለሁ ተብሎ ይታሰባልን? በተጨማሪም ወልቃይትን ለህወሓት አስረክቦ የኢትዮጵያን ሉዐላዊነት ማስከበርስ ይቻላልን? 2. በአማራው ላይ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ፣ በሰሜን እዝ ላይ ወረራ፣ የአፋር ህፃናትና ተፈናቃይ ሴቶችን በጅምላ የፈጀው፣ በሺህ የሚቆጠሩ ሴቶች ላይ አስገድዶ መድፈር የፈፀመው ህወሓት ከፖለቲካ ተሳትፎው በህግ እንደታገደ እንዲቀጥል እንጠይቃለን። 3. ህወሓት በሦስት ዙር ወረራው ከአማራና አፋር ክልሎች የዘረፈውን መጠነ ሰፊ ሀብትና ንብረት እንዲመልስ እንዲደረግ እንዲሁም፣ በ27 አመት የስልጣን ዘመኑ ስልጣኑን መከታ አድርጎ ያለ አግባብ የአገሪቱን ሀብት ዘርፎ ኤፈርት በሚል ግዙፍ ኩባንያ ያከማቸው ሃብት በአማራና አፋር ክልሎች በወራሪው ህወሓት ለወደመው መሰረተ ልማት መልሶ ግንባታ እንዲውል በአፅንዖት እንጠይቃለን። 4. ከህወሓት ጋር በሚደረጉ ቀጣይ ድርድሮች የአማራና አፋር ክልል ወኪሎች በቀጥታ እንዲሳተፉ እንጠይቃለን። በቅርቡ የአማራው ወኪሎች በደቡብ አፍሪካ በተደረገው ድርድር ለመሳተፍ ጥያቄ አቅርበው እንደነበር የሚታወስ ሲሆን በቀጣይ ድርድሮች እነዚህ ወኪሎች እንዲሳተፉ እየጠየቅን የዓለም አቀፍ የአማራ ህብረት እነዚህን የአማራ ወኪሎች እንደሚደግፋቸውም ለማሳወቅ እንወዳለን። 5. በጦርነቱ ቀጥተኛ ጉዳተኛ የሆኑት አፋር አማራና ትግራይ ክልሎች ያለ ምንም አድልዖ ጊዚያዊ አርዳታና የመልሶ ማቋቋም ድጋፍ በፍጥነት እንዲያገኙ እንጠይቃለን። 6. በኢትዮጵያ ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም እንዲመጣ የዚህ ሁሉ ሶቆቃና ችግር ዋነኛ ምንጩ ህወሓት ኢትዮጵያን ለማፍረስ እንዲመቸው በተንኮል የቀረፀው ህገ መንግሥት መሆኑን አብዛኛው ኢትዮጵያውያዊ የሚያምንበት ሀቅ ነው። ስለዚህ ላለፉት ዓመታት እየተጠየቀ ምንም ለውጥ ሳይደረግበት ጊዜው ቢባክንም አሁንም ነገ ዛሬ ሳይባል አዲስ ህገ መንግሥት የማዘጋጀቱ ሂደት እንዲጀመር በድጋሜ እንጠይቃለን። አዲስ ህገ መንግሥት በህዝቡ ተሳትፎ ሲፀድቅ ህወሓት ያዋቀረው የጎሳ ፌደራሊዝም ተወግዶ ሁሉንም የፌደራል አወቃቀር መርሆዎችን እና የዜጎችን መብት ዋነኛ መሰረት ያደረገ የፌደራል ስርዓት ሲዘረጋ አሁን የሚታየው የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ ተወግዶ ሰላማዊ ጊዜ በኢትዮጵያ ይመጣል ብለን እናምናለን። ለአማራ ክልል መንግሥትና የአማራ ክልል ምክር ቤት አባላት:_ 1. ክልሉን በመምራት ላይ የምትገኙ የክልሉ መንግሥትም ሆነ የምክር ቤት አባላት አሁን አማራው የደረሰበት ነገር ከምንጊዜውም በላይ የገዘፈና የከፋ ችግር መሆኑን ተገንዝባችሁ የታሪክ ተጠያቂ እንዳትሆኑ ብቻ ሳይሆን በተደጋጋሚ የተከዳ ህዝብ የንዴትና ቁጭት ማእበል እንዳይፈጠርና ከተፈጠረ በቅድሚያ ወላፈኑ የሚያገኘው እናንተን በመሆኑ ከዚህ የህልውና አደጋ ከተጋረጠበት ህዝብ ጎን በመቆም ታሪካዊ የሆነ አመራር እንድትሰጡ እንጠይቃለን፣ እንመክራለን። ይህን መነሻ በማድረግ፦ በህግ የማስከበር ዘመቻ በሚል ሽፋን የታሰሩ ፋኖዎች፣ ወጣቶች፣ የልዩ ኃይል አባላት፣ ሚሊሻወች፣ የማህበረሰብ አንቂወች፣ የፖለቲካ መሪዎች፣ ጋዜጠኞች፣ የሲቪክ ማህበራት መሪዎች፣ አርበኛ ፋኖ ዘመነ ካሴን ጨምሮ ሁሉንም በዚህ አግባብ የታሰሩ ሁሉ በአስቸኳይ በመፍታት አማራው በአንድነት በመሆን ለተጋረጠበት የህልውና አደጋ መፍትሄ እንዲያፈላልግ፣ 2. በአሁኑ ሰዓት የአማራው አንድነት አጅግ አስፈላጊ በመሆኑ አማራውን በመንደርተኝነት በመከፋፈል ለማዳከም የሚጥሩ ኃይሎችን ከውስጣችሁ እንድታጠሩ፣ 3. ወልቃይትና ራያ ለአማራው ቀይ መስመር ናቸው ሲባል እንዳልነበረ ሁሉ አሁን አማራው ባልተሳተፈበት ህዝ መንግሥትና ከህገ መንግሥቱ መፅደቅ በፊት በጉልበት ተወስደው የነበሩት አሁንም የፓለቲካ ቁማር መጫወቻ ሲሆኑ ምን ተሰማችሁ? ይህንን ለመቀልበስ ከባድ መስዋእትነት ከእናንተና ህዝቡ ይጠበቃል። መሪ ማለት በቃሉ የሚገኝ ብቻ ነው። አበው እንደሚሉት የተናገሩት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ ይባል አይደል። ስለዚህ የፌደራል መንግሥት አንድ አካል ስለሆናችሁ ይህ ቀይ መስመራችን ነው እንዳላችሁ አሁንም ይህን አቋም ብትገፉበት ድፍን የአማራ ህዝብ ከጎናችሁ ይቆማል፣ የህዝቡም ጥያቄ ተገቢውን መልስ ያገኛል የሚል እምነት አለን። ለአማራ ህዝብ:_ 1. በዚህ አምሳ አመት ውስጥ ምን ያልደረሰብህ ነገር አለ? በህወሓት 27 አመት የስቃይ ዘመን ስንቱን ግፍ አሳልፈሃል? ይባስ ብሎ ለውጥ ለማምጣት እንዳልተዋደቅህ ሁሉ በአንተ ልጆች ደም ውጤት ስልጣን የጨበጡት መሪወች እንደሌለህ ቆጥረውህ በዚህ መሪር የአራት አመት ጊዜ ውስጥ የተቀበልኸውን መከራ ለመዘርዘርም ያስፈራል። ስለምታውቀው ለቀባሪው ማርዳት እንዳይሆንብን እናልፈዋለን። ዋናው ነገር ከዚህ ሁሉ መከራ በአሸናፊነት ለመወጣት ውስጣዊ አንድነትህን በማጠናከር ጠንካራ አደረጃጀት መፍጠር ነው። አንተ ባልተሳተፍህበት ድርድር የተደረሰ እና ፍትሃዊ ያልሆነ ስምምነት የመቀበል አንዳችም ግዴታ የለብህም። ወልቃይትንና ራያን በደምህና በከፈልኸው መስዋዕትነት በእጅህ ይዘሃል፣ ጠንክረህ ይዞታህን ጠብቅ! ሌሎች የማንነት ጥያቄወችህን በመተከል፣ በደራ እንዲሁም የህገ መንግሥትን ለውጥ ጨምሮ በጊዜያቸው ምላሽ እንድታገኝ ጠንክረህ በመደራጀት ታገል! ህልውናህን የምታስከብረው በራስህ ጥንካሬ ስለሆነ የቁርጥ ቀን ደራሽህን ፋኖን በደንብ ደግፍ! እኛ በውጭ የምንገኝ ልጆችህም ለህልውናህ፣ ለእኩልነትና ፍትህ ለማስፈን ለምታደርገው ትግል ከጎንህ የምንቆም መሆኑን ልናረጋግጥልህ እንወዳለን። ድል ለተገፋውና በተደጋጋሚ ለተከዳው አማራ ኢትዮጵያ በሀቀኛ ልጆች ትግልና መስዋዕትነት ታፍራና ተከብራ ትኖራለች።

Source: Link to the Post

Leave a Reply