በአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ አብን አባላትና አመራሮች ላይ የሚፈፀመው እስር፣እንግልትና ወከባ እንደቀጠለ መሆኑ ተገለፀ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ጥቅምት 18 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ አ…

በአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ አብን አባላትና አመራሮች ላይ የሚፈፀመው እስር፣እንግልትና ወከባ እንደቀጠለ መሆኑ ተገለፀ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ጥቅምት 18 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች ዛሬ ይደረጋል የተባለውን የተቃውሞ ሰልፍ ተከትሎ የፀጥታ አካላት በአብን አመራሮችና አባላት ላይ ያልተገባ እንግልት እየፈፀሙ ነው ተብሏል። እንደአብነትም የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ አብን አባል የሆነው አስፋው ፍስሀ ዛሬ ጥቅምት 18 ቀን 2013 ዓ.ም አብን የጠራው የተቃውሞ ሰልፍ እንዲደረግ አስተባብርሀል በሚል ጠዋት በገንዳ ውሀ የልዩ ኃይል ካምፕ ስለመታሰሩ ነው የደረሰን መረጃ ያመለከተው። በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውሀ ከተማ ዛሬ ጠዋት ላይ ትፈለጋለህ በሚል ወደ ልዩ ኃይል ካምፕ ተወስዶ መታሰሩ ተገልጧል። በአማራ ክልል ከተሞች ይደረጋል የተባለውን በአማራ ላይ የሚፈፀመው የዘር ማጥፋት ወንጀል እንዲቆም የሚጠይቀው የተቃውሞ ሰልፍን በተመለከተ የማስተባበሪያ ጽ/ቤቱ አመራሮች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተነጋግረውበት እንደነበር ተሰምቷል። አስፋው ፍስሀ በተለያዩ ጊዜያት በዞኑም ሆነ በዙሪያ ወረዳዎች የሚታዩ ችግሮች/ ብልሹ አሰራሮች እንዲስተካከሉ በሚል ማጋለጡ እንዳልተወደደለትና ከማስፈራራት አልፎ እስከ መታሰር አድርሶት እንደነበር ይታወሳል። ዛሬ ይደረጋል የተባለውን ሰልፍ ተከትሎ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የክልሉን መንግስት ጨምሮ ዞን፣ከተማ መስተዳደሮችና ወረዳዎች ሳይቀር የተለያዩ የክልከላ መግለጫዎችን ሲያወጡ ተስተውሏል። በአዊ ብሄረሰብ ዞን በዳንግላ፣ በዱር ቤቴ እና በተለያዩ አካባቢዎችም የሰልፍ አስተባባሪዎችን ማሰር፣ማዋከብና ለማስፈራራት መሞከርም እንደነበር ይታወቃል። በተመሳሳይ የድሞው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ብሔራዊ ምክር ቤት አባል የነበሩት አቶ ገዛኸኝ መርሻ ዛሬ ጥዋት ቡሬ ከመኖሪያ ቤታቸው በፖሊስ ታፍነው ተወስደዋል ሲሉ የምዕራብ ጎጃም ዞን የአብን ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ም/ሰብሳቢ አቶ አሸናፊ አካሉ በገጻቸው አስፍረዋል። በባህር ዳር በሰላማዊ ሰልፈኛ ላይ ድብደባ መፈፀሙን፣በሰሜንና ደቡብ አቸፈርም አመራሮች ላይ ያልተገባ ወከባ መፈፀሙን ገልፀዋል። በአንጻሩ በራያ ቆቦ የተሳካ የሚባል ሰላማዊ ሰልፍ ስለመደረጉ በማህበራዊ ሚዲያ እየወጡ ያሉ መረጃዎች አመልክተዋል። አብን በዚህ ስርዓታዊ የአፈና ሁኔታ ሆኖ ሰልፉን ለማስተባበር እንደማይችል መግለፁን ተከትሎ በገንዳ ውሀ ከተማ የተደረገ ሰልፍ አለመኖሩን፣ በአስፋው መታሰር የከተማው ወጣቶች ከፍተኛ ቅሬታ እንደተሰማቸውና ለማስፈታትም በማስተባበሪያ ጽ/ቤቱ በኩል ጥረት እየተደረገ ስለመሆኑ ለማወቅ ተችሏል። አማራ ሚዲያ ማዕከል የሚመለከተውን የፀጥታ አካልና ሰልፈኞችንም በማነጋገር እንቅስቃሴው ምን እንደሚመስል ዘገባውን አጠናቅሮ የሚመመለስ ይሆናል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply