በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ ህግ የማስከበር ዘመቻ በሚል ሰዎች ከህግ አግባብ ውጭ እየታሰሩ መሆኑ ተገለጸ፤ በአንዳንድ አካባቢዎች ይህ እስር አስገድዶ የመሰወር ድር…

በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ ህግ የማስከበር ዘመቻ በሚል ሰዎች ከህግ አግባብ ውጭ እየታሰሩ መሆኑ ተገለጸ፤ በአንዳንድ አካባቢዎች ይህ እስር አስገድዶ የመሰወር ድርጊት እንደነበረም ኢሰመጉ በሪፖርቱ አመላክቷል። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ጳጉሜ 3 ቀን 2014 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ በአማራ ክልል ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጪ በመሆን ፖሊስ ጣቢያዎች እና ማረሚያ ቤቶች በዋስ እንዲለቀቁ የተወሰነላቸውን ተጠርጣሪዎች ከህግ አግባብ ውጪ ይዘው እንደሚያቆዩ ኢሰመጉ ገልጧል። ችግሩ እየታየባቸው ያሉ በተለይም አማራ፣ኦሮሚያና አዲስ አበባን ጨምሮ በመግለጽ የክልል መንግስታት እንዲሁም የፌደራል መንግስት ከእዚህ መሰል ድርጊት እንዲቆጠቡ እና ማሻሻያ እርምጃዎችን እንዲወስዱ ሲወተውት ስለመቆየቱም ኢሰመጉ አውስቷል፡፡ ሀምሌ 22 ቀን 2014 ዓ.ም በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት በዋለው ችሎት መሰረት ዶ/ር ወንድወሰን አሰፋ፣ ኢንጅነር በየነ አልማው፣ ሻለቃ ስጦታው መልኬ፣ ገበየሁ ሞላ፣ ዶ/ር ታደሰ፣ አበበ ሙላቱ፣ ኢሳያስ ደመቀ፣ ታደሰ ፍቅረ፣ ሽታየ የትዋለ፣ ጌታሁን በሬ፣ አትንኩት ሰርጸድንግል፣ ሰዋሰው አረጋው እና ናትናኤል አበባው የተባሉ 14 ሰዎች እያንዳንዳቸው በ25,000 ብር ዋስ ከእስር እንዲለቀቁ ስለመወሰኑ ጠቅሷል። ይሁን እንጅ ሀምሌ 23 ቀን 2014 ዓ.ም የፌደራል ፖሊስ ወደ አዲስ አበባ ይዞ ለመሄድ ባደረገው ሙከራ ባህር ዳር ከተማ ሳባታሚት ማረሚያ እና አካባቢው ላይ ውጥረት ተፈጥሮ እንደነበርም አውስቷል። በዚህም ምክንያት ፌደራል ፖሊስ ይዞ መሄድ አለመቻሉን እና ፍርድ ቤት በዋስ እንዲወጡ የወሰነላቸው 14 ሰዎች ይህ መግለጫ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ በእስር ላይ መሆናቸውን ኢሰመጉ ባሉበት ማረሚያ ቤት በመሄድ ለማረጋገጥ መቻሉን አስታውቋል፡፡ በተጨማሪም ኮማንደር ምላሹ አስግደዉ ጓንጉል እና ም/ኮማንደር ቀኘ ገ/መስቀል ወ/አረጋይ የተባሉ ሁለት የአማራ ልዩ ሃይል አባላት ታህሳስ 2014 ዓ/ም ጀምሮ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረዉ ከተደጋጋሚ የጊዜ ቀጠሮ በኋላ በየካቲት 2014 ዓ/ም በዋስ እንዲለቀቁ የባህር ዳርና አካባቢዉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ቢወስንም አቃቢ ህግ በመቃወሙ ዋስትና ተከልክለዉ ይህ ሪፖርት እስከወጣበት ጊዜ ድረስ ለ9 ወራት ያለምንም የፍርድ ቤት ትዕዛዝ እና ክስ ማረሚያ ቤት እንደሚገኙ ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ኢሰመጉ አፋርን ጨምሮ በአማራ የተለያዩ አካባቢዎች በግፍ እስር ላይ ስለሚገኙት ፋኖዎች፣አባላት፣ደጋፊዎች እና ወዳጆች ጉዳይ በሪፖርቱ ዝርዝር ነገር ከማካተት ተቆጥቧል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply