በአማራ ክልል በአሸባሪው ህወሓት ወረራ ምክንያት ከ260 በላይ ትምህርት ቤቶች ሙሉ ለሙሉ ወደሙ፡፡

አዲስ አበባ፣ መስከረም 3፣ 2014 በአማራ ክልል በአሸባሪው ህወሓት ወረራ ምክንያት ከ260 በላይ ትምህርት ቤቶች ሙሉ ለሙሉ ወደሙ፡፡ በአሸባሪው የህወሓት ወረራ ምክንያት ከ260 በላይ ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ ሲወድሙ 2 ሺህ 511 የሚደርሱ ትምህርት ቤቶች ደግሞ በከፊል ጥቃት እንደደረሰባቸው የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፡፡

በአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት እና ጽሕፈት ቤት ሀላፊ አቶ ጌታቸው ቢያዝን እንዳሉት አሸባሪ ቡድኑ ክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች በከፈተው ወረራ ከቅድመ መደበኛ እስከ ኮሌጅ ድረስ ያሉ የትምህርት ተቋማትን አውድሟል፡፡ በዚህም እስካሁን ከ260 በላይ ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ ወድመዋል፤ 2 ሺህ 511 የሚደርሱ ትምህርት ቤቶች ደግሞ በከፊል ጥቃት እንደደረሰባቸው ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

በቅርብ ጊዜ መረጃዎቹ ሲጣሩ የጉዳቱ መጠን ከዚህ የከፋ እንደሚሆን ይገመታል ያሉት ሀላፊው፤ ጉዳት የደረሰባቸው ትምህርት ቤቶች ከ1 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን ያስተናግዱ የነበሩ እንደሆነም ገልፀዋል፡፡ አሸባሪው ህወሓት በሁሉም ትምህርት ቤቶች የነበሩ የመማር ማስተማሪያ ግብዓቶችን ዘርፏል፤
ማንቀሳቀስ ያልቻለውን ደግሞ ጥቅም በማይሰጥ መልኩ አውድሟል ብለዋል፡፡ የ2014 ዓ.ም የትምህርት ዘመን በቅርቡ እንደሚጀመር የገለጹት ሀላፊው፤ ነፃ በወጡ አካባቢዎች ያለውን የጉዳት መጠን የሚያጠና ቡድን ወደ አካባቢዎቹ እንደተላከም ጠቁመዋል፡፡በተቋማቱ ላይ የደረሰውን የጉዳት መጠን በመለየት የመልሶ ግንባታ ሥራዎችን በቅርቡ ለመጀመር እየተሠራ እንደሆነ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ማስታወቁን አሚኮ ዘግቧል፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply