በአማራ ክልል ትልልቅ ከተሞች ታግዶ የነበረው የዳታ ኢንተርኔት አገልግሎት መለቀቁ ተሰማ

አርብ ግንቦት 4 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በአማራ ክልል ከልዩ ኃይል እንደገና መደራጀት ጋር ተያይዞ በተከሰተው አለመግባባት በትልልቅ ከተሞች የኢንተርኔት አገልግሎት ተቋርጦ እንደቆየ የሚታወቅ ሲሆን፣ ካሳለፍነው ረቡዕ መጋቢት2/2015 ምሽት ጀምሮ አገልግሎቱ መለቀቁን አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡

የዳታ ኢንተርኔት አገልግሎት ተቋርጦባቸው የነበሩት ጎንደር፣ ባህርዳር እና ወልዲያ ከዕረቡ ምሽት ጀምሮ መስራት እንደጀመረ ታውቋል፡፡

መንግሥት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጉዳይ ጋር በተገኛኘ ተፈጥሮ በነበረው ውጥረት የዳታ ኢንተርኔት ደገብ ከጣለ ከሦስት ወራት በላይ አስቆጥሯል፡፡ ይሁን እንጂ በተለይ በትልልቅ ከተሞች የሚኖሩ ዜጎች የኢንተርኔት አግልግሎቱን በቪፒኤን አማካኝነት እየተጠቀሙ ይገኛሉ፡፡

በአንዳንድ አካባቢዎች በቪፒኤን የሚሰራው የዳታ ኢንትርኔት አግልግሎት ሙሉ በሙሉ ሲቋረጥ ይታያል፡፡ አማራ ክልል ከእነዚህ አካባዎች አንዱ ሲሆን፤ በኢንተርኔት መዘጋት በርካቶች ሥራቸውን መስራት እንዳልቻሉ እና ከቤተሰቦቻቸው ጋር መገናኘት ባለመቻላቸው ለኢትዮቴሌኮም በተደጋጋሚ ቅሬታቸውን እያቀረቡ እንደነበርም ገልጸዋል፡፡

የሞባይል ዳታ አገልግሎት በአማራ ክልል በጎንደር፣ በባህርዳር እና በወልዲያ ከተማ ከተዘጋ ከኹለት ሳምንታት በላይ ያስቆጠረ ሲሆን፣ የተዘጋበት ዋና ምክንያት በክልሉ ከሚንቀሳቀሰው ታጣቂ ኃይልና ከክልሉ ልዩ ኃይል ጋር በተገናኘ በተፈጠረው ውጥረት ነው፡፡

በእነዚህ ከተሞች ሲካሄድ የነበረው ሰላማዊ ሰልፍ፣ መንገድ መዝጋትና አለመግባባት ችግሩ በመቀረፉ እንዲሁም መንግሥት ከፋኖ አባላት ጋር መግባባት ላይ በመድረሱ እና በከተማዎቹ ሰላም በመስፈኑ የኢንተርኔት አገልግሎቱ እንደተለቀቀላቸው ነዋሪዎቹ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

The post በአማራ ክልል ትልልቅ ከተሞች ታግዶ የነበረው የዳታ ኢንተርኔት አገልግሎት መለቀቁ ተሰማ first appeared on Addis Maleda.

Source: Link to the Post

Leave a Reply