በአማራ ክልል የቀጠለው የትጥቅ ግጭት እና በሲቪል ሰዎች ላይ ከሕግ ውጭ የተፈጸሙ ግድያዎች አሳሳቢ ሆኗል አለ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን

በሰሜን ጎጃም ዞን መራዊ ከተማ በርካታ ንጹሃን በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች መገደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን አስታወቀ።

ኢሰመኮ ባወጣው መግለጫ፥ በከተማዋ ጥር 20 ቀን 2016 ዓ.ም በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በታጠቁ ኃይሎች (በተለምዶ ፋኖ በመባል የሚጠሩት) መካከል ከጠዋቱ 12፡00 ሰዓት አካባቢ ጀምሮ ውጊያ መካሄዱን አስታውሷል።

የመንግስት ጸጥታ ኃይሎች በመራዊ “ለፋኖ ድጋፍ አድርጋችኋል” በሚል ቢያንስ 45 ንጹሃንን ገድለዋል ብሏል ኢሰመኮ

“የፋኖ አባላት ናቸው” በሚል ተጠርጥረው የተያዙና ለጊዜው ብዛታቸውን ለማረጋገጥ ያልተቻለ ሰዎች በተመሳሳይ በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች መገደላቸውንም ኮሚሽኑ ገልጿል

በሸበል በረንታ እና ቋሪት ወረዳዎችም ከ21 በላይ ሲቪሎች በጸጥታ ሃይሎች መገደላቸው በኮሚሽኑ መግለጫ ተጠቅሷል

ኮሚሽኑ በሲቪል ሰዎች ላይ ስለደረሰው ጉዳት ምርመራ እያከናወነ ቢሆንም፤ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ምላሽ ያልሰጡ በመሆኑ፣ በጸጥታው ሁኔታና ልዩ ልዩ ተዛማጅ ምክንያቶች ሙሉ መረጃዎች ገና በተሟላ ሁኔታ ማሰባሰብ ባለመቻሉ የምርመራ ስራው በተሟላ መልኩ ሊጠናቀቅ አለመቻሉን ጠቅሷል።

ኢሰመኮ እስካሁን ድረስ ባደረገው ክትትልም የመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች ማንነታቸውን ማረጋገጥ የቻላቸውን ቢያንስ 45 ሲቪል ሰዎች “ለፋኖ ድጋፍ አድርጋችኋል” በሚል ከህግ ውጭ መግደላቸውን ነው የገለጸው።

ኮሚሽኑ ከደረሱት በርካታ ጥቆማዎችና ከልዩ ልዩ መረጃ ምንጮች ከተሰበሰቡት የሲቪል ሰዎች ስም ዝርዝር ውስጥ እስካሁን ድረስ ማንነታቸውን በመለየት ለማረጋገጥ የተቻለው 45 ሲቪል ሰዎችን ብቻ ቢሆንም የጉዳቱ መጠን ከዚህ ሊበልጥ እንደሚችል ምክንያታዊ ግምት መውሰድ ተችሏልም ነው ያለው።

ከዚህም ባሻገር “የፋኖ አባላት ናቸው” በሚል ተጠርጥረው የተያዙና ለጊዜው ብዛታቸውን ለማረጋገጥ ያልተቻለ ሰዎች በተመሳሳይ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ከህግ ውጭ መገደላቸውን ጠቁሟል።

ለቀን ሥራ በጠዋት ከቤታቸው ወጥተው ድንገት ተኩስ ሲከፈት በአንድ ቦታ ተጠልለው የነበሩ 18 ሲቪል ሰዎች መገደላቸውን ምስክሮች ነግረውኛል ያለው ኢሰመኮ፥

ቀበሌ 02 አካባቢ በተለምዶ ሚሊኒየም ተብሎ በሚጠራ ሰፈር አንድ የጠፋ አባልን ሲያፈላልጉ የነበሩ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች “በፍለጋው አልተባበሩም” ያሏቸውን 8 ሲቪል ሰዎችን መግደላቸውንና 12 ባጃጆችን ማቃጠላቸውን እንደገለጹለት በመግለጫው አብራርቷል።

በሌላ በኩል በምሥራቅ ጎጃም ዞን ሸበል በረንታ ወረዳ የዕድውኃ ከተማ 15 ሲቪሎች (ሴቶችን) ጨምሮ፤ በምዕራብ ጎጃም ዞን፣ ቋሪት ወረዳ ደግሞ 6 ሲቪል ሰዎች በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ከሕግ ውጭ መገደላቸውን ምስክሮች ለኢሰመኮ ማስረዳታቸው በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ በአማራ ክልል በቀጠለው ግጭት በሲቪል ሰዎች ላይ እየደረሰ ያለው ስቃይ እጅግ እየጨመረ መምጣቱን በመጥቀስ ከሕግ ውጭ የሚፈጸም ግድያ ሙሉ በሙሉ እንዲቆምና ለዘላቂ መፍትሄ ሁሉም ወገኖች ሰላማዊ ውይይትን በቁርጠኝነት እንዲቀበሉ ጠይቀዋል።

ኮሚሽኑ የተሟላ ምርመራ ተደርጎ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥና የተበደሉም እንዲካሱ አሁንም በድጋሚ ጥሪውን ያቀርባል ነው ያሉት።

የካቲት 05 ቀን 2016 ዓ.ም

Facebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Source: Link to the Post

Leave a Reply