በአማራ ክልል የቀጠለው ግጭት የማህበረሰብ ግንኙነትን በከፋ ደረጃ እያሻከረ መሆኑ በጥናት ተገለጸ

በክልሉ ያለውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያግዛል የተባለ መድረክ ተካሄዷል 

በአማራ ክልል ከሰባት ወራት በላይ የዘለቀውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ሚና ይኖረዋል የተባለ መድረክ ዛሬ መጋቢት 3 ቀን 2016 በአዲስ አበባ ተካሄዷል። 

የኢትዮጵያ ሰላም ተቋም እና ዩ.ኤስ.ኤ.አይ.ዲ ባዘጋጁትና ከሰላም ሚኒስቴር፣ ከአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮን ጨምሮ የተለያዩ ተወካዮች፣ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር እና ሌሎች ተሳታፊዎች በተገኙበት መድረክ በአማራ ክልል ግጭቶች ላይ ያተኮረ ጥናት ቀርቧል። 

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም እና የሰላም ሚኒስቴር በጋራ በአገር አቀፍ ደረጃ እየተደረገ ከሚገኝ ምርምር ላይ በአማራ ክልል ዙሪያ ያተኮረው ክፍል ቀርቧል። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ተባባሪ ፕሮፌሰር ደሳለኝ አምሳሉ እንደገለጹት በጥናቱ መሰረት ከፈረንጆች 2001 እስከ 2023 ድረስ በኢትዮጵያ በሺዎች የሚቆጠሩ ግጭቶች ተከስተዋል። 

ከነዚህም ውስጥ 44 በመቶ የሚሆነው በጦር ሜዳዎች የሚደረጉ የትጥቅ ትግል መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን 23 በመቶ የሚሆነው በንጹሀን ላይ ታጣቂዎች የሚፈጽሙት ጥቃት እንዲሁም 17 በመቶ ደግሞ አመጾች መሆናቸው በጥናቱ ተመላክቷል። 

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጣር በ2023 ዓመት ብቻ 689 ግጭቶች በአማራ ክልል ተከስቷል። በአንጻሩ በቆዳ ስፋት ከአማራ ክልል የሚልቀውና በቀደሙት ዓመታት የከፋ የሰላም እጦት ውስጥ የሚገኘው ኦሮሚያ ክልል በ2023 ሙሉ ዓመት 672 ግጭቶን እንዳስተናገደ በጥናቱ ተገልጿል። 

የጥናት ባለሙያው ተባባሪ ፕሮፌሰር ደሳለኝ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት መረጃ የማይገኝባቸው ጉዳዮች ሊኖሩ እንደሚችሉ ጠቅሰው በጥናቱ የተጠቀሱት “ቁጥሮቹ ከዚህ ቢበልጡ እንጂ ሊያንስ እንደማይችል ይጠበቃል” ብለው በአጠቃላይ ግኝቱ ግጭት ተፈጥሯዊ ነው ብቻ ብሎ ማለፍ የሚቻልበት ሁኔታ እንዳልሆነ ያሳያል ሲሉ አሳሳቢነቱን አመልክተዋል። 

በዓመቱ ከተከሰቱ ግጭቶች በአማራ ክልል ዋና ከተማ ባህር ዳር የሚገኝበት ምዕራብ ጎጃም ዞን 143 ግጭቶችን ማስተናገዱ በጥናቱ ተገልጿል። ሰሜን ሸዋ ዞን 139 እንዲሁም ሰሜን ወሎ ዞን 126 ግጭቶችን በማስተናገድ ቀዳሚ አካባቢዎች ሆነዋል። በአንጻራዊነት ከክልሉ አካባቢዎች ሰሜን ጎንደር፣ አዊ፣ ዋግ ኽምራ አካባቢውች ሠላማዊ ናቸው ተብሏል። በአጠቅላይ በዓመቱ ብቻ በክልሉ 22 የድሮን ጥቃቶች መፈጸማቸው ተገልጿል። 

በሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታና ብሔራዊ መግባባት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ኸይረዲን ተዘራ “በአገራችን የተፈጠሩ የትኛውም የሰላም ጉዳዮች ያለዕድል ሆኖ የአገሪቷን የረጅም ዕድሜ ታሪክ በማይመጥን መልኩ፤ በአንድ በኩል ችግሮችን ቁጭ ብለን ለመፍታት በየአካባቢያችን ባህል ቢኖረንም በሌላ በኩል በዘመናዊ የፖለቲካ ታሪካችን ውስጥ ግን” ችግሮችን በጉልበት ለመፍታት ሲሞከር ይስተዋላል ብለዋል።

በአገሪቱ ያሉት ሁሉም ችግሮች በአማራ ክልልም ሆነ ኦሮሚያ ክልል ሆነ የተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች “ማንኛውም አካል እንደግልም እንደቡድንም” የሚነሱ ጥያቄዎች ቁጭ ብሎ “በመነጋገር ብቻ ለመፋታት መንግስት ሁሌም ክፍት ነው” ሲሉም ሚኒስትር ዲኤታው ገልጸዋል።

አዲስ ማለዳ በተከታተለችው መድረክ የኢትዮጵያ ሰላም ተቋም የቦርድ ዳይሬክተር አምባሳደር ሙሉጌታ ኢተፋ በበኩላቸው “አገራችን በአስቸጋሪ ጊዜ ውስጥ ትገኛለች፤ ለምን ያህል ጊዜ እየተገዳደልን እና ወንድም የውንድሙን ደም እያፈሰሰ ይቀጥላል? ለምንስ ያህል ጊዜ ለዘመናት ሀብት የፈሰሰባቸው የህዝብ መሰረተ ልማቶች እየፈረሱ ይቀጥላሉ? ቂምና ቁርሾን ለቀጣዩ ትውልድስ እስከመቼ ድረስ እናስተላልፋለን?” ሲሉ የግጭቶችን አስከፊነት ጠቁመዋል። 

በአሜሪካ ተራድዖ ድርጅት የኢትዮጵያ ቢሮ የዲሞክራሲና አስተዳደር ቢሮ ዳይሬክተር ስቴፋኒይ ግሬቪ ኢትዮጵያ በተለያዩ ክልሎች በግጭት እየታመሰች ነው ብላ፤ በአማራ ክልል ተማሪዎች ከትምህርት ርቀዋል፣ አርሶ አደሮች ማረስ እየቻሉ ባለመሆኑ በጤፍና መሰል ንግዶች ዋጋ መናር የምግብ ዋስትና እየተፈተነ እንደሚገኝ ተናግራለች። በተጨማሪም መሰረታዊ የጤና ግብዓቶችን ማጓጓዝ እጅግ አስቸጋሪ በመሆኑ የክልሉ ነዋሪዎችን አደጋ ውስጥ እያስገባ መሆኑን አጽንዖት ሰጥተዋል። 

የኢትዮጵያ ሰላም ተቋም የቦርድ ዳይሬክተር አምባሳደር ሙሉጌታ ኢተፋ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ያሉ ግጭቶች የህዝብ አንድነትን እየሸረሸሩ መሆኑን ጠቅሰው በመላው አገሪቱ ቀጣይ መድረኮች ይካሄዳሉ ብለዋል። በአገሪቱ ውስጥ ያሉና በየጊዜው የሚከሰቱ ግጭቶች በሙሉ በንግግርና በድርድር ብቻ እንዲፈቱ ያተኮረ ስራ ይሰራል ያሉት አምባሳደር ሙሉጌታ ለሰላም የሚደረጉ ጥረቶች በምንም መልኩ ተስፋ ሊቆረጥባቸውና ሊቋረጡ አይገባም ሲሉ አሳስበዋል። 

በቀረበው ጥናት መሰረት ግጭቶቹ በቀላሉ የማይለቁ እና ለረጅም ጊዜ ሊቆዩ የሚችሉ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን በትጥቅ ትግል መጨመርና መባባስ እንዲሁም የግጭቱ ተሳታፊዎችና አሰላለፍ ግልጽ አለመሆን ይበልጥ ውስብስ አድርጓቸዋል ተብሏል።

በጥናቱ መሰረት ግጭቶቹ የሰዎችን ህይወት ከማጨለማቸው ባለፈ፤ በህይወት የመኖር መብትን ይጋፋሉ፣ ለአካል ጉዳት ይዳርጋሉ፣ ምጣኔ ሀብትን ያንኮታኩታሉ፣ መሰረተ ልማት ያወድማሉ፣ ዜጎችን ከመኖሪያቸው ያፈናቅላሉ፣ የማህበረሰብ ግንኙነቶችን ያሳሳሉ። በግጭት ሳቢያ የህብረተሰብ ግንኙነትና አንድነት መሳሳት በአማራ ክልል በከፍተኛ ደረጃ እየታየ መሆኑም በጥናቱ ተገልጿል።

በክልሉ ያለው ግጭት ሁኔታ አገራዊ እሴቶችን የሚያረክስ፣ በተራዘመ ግጭት ብሶት እና ሌላ ግጭት መፍጠር፣ ለውክልና ጦርነትና ለውጭ ኃይሎች ጣልቃ መግባት እድል መፍጠር የሚዳርጉ ናቸውም ተብሏል። በተጨማሪም ለአብዛኛዎቹ ግጭቶች የፖለቲካ ሽግግር ወቅት፣ የምርጫ እና የፖለቲካ ድርጅቶች ምስረታ ወቅቶች ዋነኛ መነሻ ነጥቦች መሆናቸው ተገልጿል። 

የሰላም ሂደቶችን በአፋጣኝ መጀመር፣ ተያያዥነት ያላቸው ግጭቶች በመሆናቸው በሰላማዊ ንግግር በዘላቂነት አዙሪቱን ማቋረጥ፣ ግጭቶችን እንደየሁኔታቸው መፍታት እንዲሁም መዋቅራዊ የግጭት መንስዔዎችን በንግግር መቅረፍ በዘላቂነት ሰላም ለማስፈን በጥናቱ ከተጠቆሙ መፍትሄዎች መካከል ናቸው።     

“የግጭቶቹ ውጤት በሰው አዕምሮ ውስጥ የሚቀሩ በመሆናቸው ያንን መሻር የሚቻለው ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ ከተፈቱ ብቻ ነው” ሲሉም የጥናት ባለሙያው ተባባሪ ፕሮፌሰር ደሳለኝ አምሳሉ ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ሰላም ተቋም ላለፉት 35 ዓመታት ግጭቶች እንዳይከሰቱ፣ ከተከሰቱም በንግግር እንዲፈቱ ሚና መጫወት እንዲሁም የማህበረሰብ ትስስርን የሚያጠናክሩ ስራዎች እየሰራ የሚገኝ ተቋም ነው።

Source: Link to the Post

Leave a Reply