በአማራ ክልል የዕለት ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች የሚቀርበው እርዳታ በቂ አይደለም፤ ከ6 ነጥብ 7 ሚሊየን በላይ ወገኖች ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ሲል ኮሚሽኑ አስታወቀ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ…

በአማራ ክልል የዕለት ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች የሚቀርበው እርዳታ በቂ አይደለም፤ ከ6 ነጥብ 7 ሚሊየን በላይ ወገኖች ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ሲል ኮሚሽኑ አስታወቀ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ጥር 26 ቀን 2015 ዓ/ም … አዲስ አበባ ሸዋ በአማራ ክልል ችግር ውስጥ ለሚገኙ ከ6 ነጥብ 7 ሚሊየን በላይ ወገኖች ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው የአማራ ክልል የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን አስታውቋል፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ ወገኖች ብቻ ሳይሆኑ ግጭት በነበረባቸው የክልሉ አካባቢዎች የሚገኙ ወገኖችም የምግብ አቅርቦት እንደሚያስፈልጋቸው ተገልጿል፡፡ እነዚህ ዜጎች አምርተው እራሳቸውን እስከሚችሉ ድረስ ድጋፍ ሊቀርብላቸው እንደሚገባም ነው የተመለከተው፡፡ በአማራ ክልል ከ1 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ ከተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎች መኖራቸውን የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኢያሱ መስፍን ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ ከ800 ሺህ በላይ ያህሉ የጸጥታ ችግር ካለባቸው የተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ሲሆኑ፥ 75 ሺህ ወገኖች በ40 ጊዜያዊ መጠለያዎች እንደሚገኙ እና ቀሪዎቹ ደግሞ በማህበረሰቡ ውስጥ ተጠግተው እንደሚኖሩም ነው የሚናገሩት። ከምግብ አቅርቦት አኳያም እንደክልል ከ6 ነጥብ 7 ሚሊየን በላይ ወገኖች ድጋፍ እንደሚሹ መረጃን መሰረት በማድረግ ተለይቶ ለፌደራል መንግሥት መላኩን ጠቅሰው፥ ከዚህ ውስጥ የፌደራል መንግሥት ለ3 ነጥብ 5 ሚሊየን ያህሉ መፍቀዱን ገልጸዋል፡፡ በዚህም 70 በመቶ በፌደራል መንግሥት እና 30 በመቶ ደግሞ በአጋር አካላት በኩል ድጋፉ እንዲቀርብ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡ ይሁን እንጅ ይህም ቢሆን ወቅቱን ጠብቆ በመቅረብ ረገድ ውስንነት እንዳለበት ነው አቶ ኢያሱ የተናገሩት፡፡ በመንግሥት በኩል የሚቀርበው ድጋፍ ጊዜውን ካለመጠበቁ በተጨማሪ መቅረብ የሚገባውን ድጋፍ ዓይነቶች (ፓጃኬጁን) ያሟላ አለመሆኑንም ነው ያስረዱት፡፡ በእነዚህ እና ሌሎች ተመሳሳይ ችግሮች ተፈናቃዮች እና የምግብ እጥረት ያለባቸው ወገኖች ለከፋ ችግር ተዳርገዋል ብለዋል ኃላፊው፡፡ ይህን ችግር ለመቅረፍ የክልሉ መንግሥት ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሠራ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡ የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ደበበ ዘውዴ በበኩላቸው÷ የመንግሥት ቀዳሚ ተግባር ሕይወት ማዳንን መሠረት ያደረገ ሰብዓዊ ድጋፍ ማቅረብ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ እስካሁንም በክልሉ ለ2 ሚሊየን 440 ሺህ 767 ወገኖች ድጋፉ እየቀረበ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡ ሌላው ሰሞኑን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም በአካባቢው ጉብኝት ማድረጋቸውን ተከትሎ በኮሚሽኑ አማካኝነት÷ ለአጣዬ፣ ኤፍራታ፣ አንጾኪያ፣ እንዲሁም ደብረ ብርሃን ተጨማሪ ድጋፍ መላኩን ጠቁመዋል ሲል ኤፍ ቢ ሲ ዘግቧል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply