You are currently viewing በአማራ ክልል ጅጋ ከተማ ቢያንስ 18 ሰዎች በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ገለጹ

በአማራ ክልል ጅጋ ከተማ ቢያንስ 18 ሰዎች በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ገለጹ

በሙሉጌታ በላይ

በአማራ ክልል፣ ምዕራብ ጎጃም ዞን፣ ጅጋ ከተማ፤ ቢያንስ 18 ሰዎች “በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች መገደላቸውን” አራት የከተማው ነዋሪዎች “ለኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። ብሔራዊው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)፤ “በአካባቢው ጥቃት ተፈጽሟል” የሚል መረጃ እንደደረሰው ገልጾ፤ ክስተቱን እያጣራ መሆኑን አስታውቋል።

የዓይን እማኞቹ፤ የጅጋ ከተማ ነዋሪዎች የተገደሉበት ክስተት የተፈጸመው ከትላንት በስቲያ እሁድ ሰኔ 9፤ 2016 አመሻሽ ላይ መሆኑን ገልጸዋል። በዚሁ ዕለት 11 ሰዓት ተኩል ገደማ፤ የመከላከያ ሰራዊት አባላትን የጫኑ “ሶስት ፓትሮል” ተሽከርካሪዎች ከደንበጫ ወደ ጅጋ ከተማ እየገቡ በነበረበት ወቅት፤ “በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ የፋኖ አባላት” ከፊት በነበረው መኪና ላይ ጥቃት ካደረሱ በኋላ መሸሻቸውን የዓይን እማኞቹ አብራርተዋል። 

ጥቃት ከደረሰበት መኪና ኋላ የነበሩ የመከላከያ ሰራዊት አባላት፤ በጥቃቱ “የወደቁትን አባሎቻቸውን” እነርሱ በነበሩባቸው ተሽከርካሪዎች ላይ ጭነው መሄዳቸውንም የከተማይቱ ነዋሪዎች ገልጸዋል። ከደቂቃዎች በኋላ “የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች” ወደ መሃል ከተማ በመምጣት፤ በዚያ የነበሩ ሰዎችን ጥይት በመተኮስ መግደላቸውን “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በስልክ ያነጋገረቻቸው የከተማይቱ ነዋሪዎች አስረድተዋል።  

ክስተቱን የተመለከቱ አንድ የዓይን እማኝ፤ “የመከላከያ ሰራዊት የደንብ ልብስ የለበሱ የጸጥታ ኃይሎች” በከተማው በሚገኘው ጎህ ሆቴል የነበሩ ሰዎችን “አስፓልት አስወጥተው ካሰለፏቸው በኋላ እንደገደሏቸው” ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። እኚሁ የዓይን እማኝ፤ በወቅቱ በሆቴሉ የነበሩ ፑል እና ከረንቡላ በሚጫወቱ እና በመዝናናት ላይ የነበሩ “የባንክ ቤት ሰራተኞች እና የባጃጅ አሽከርካሪዎች” እንደነበሩም ጠቁመዋል። በሆቴሉ የሚሰሩ ሴት አስተናጋጆችም፤ የሰዎቹን ማንነት “እየጮሁ ለማስረዳት” ሲሞክሩ እንደነበርም አክለዋል።

ድርጊቱ ሲፈጸም ከጎህ ሆቴል ፊት ለፊት በሚገኝ “የድንች ጥብስ ከሚሸጥበት አነስተኛ ቤት” ውስጥ ተሸሽገው ሲከታተሉ እንደነበር የገለጹ አንድ የባጃጅ አሽከርካሪ፤ “በወታደሮች ከሆቴሉ እንዲወጡ ተደርገው የተገደሉ 18 ሰዎችን”  መመልከታቸውን ተናግረዋል። “እኔ በአይኔ ያየሁት 18 የሞቱ ሰዎችን ነው። ቁስለኛ ደግሞ ሶስት ነበሩ” ሲሉ የባጃጅ አሽከርካሪው እማኝነታቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ሰጥተዋል።

ከሟቾቹ ውስጥ የሁለቱ “ቤተሰብ ጠፍቶ”፤ በማግስቱ ሰኞ ጠዋት አስክሬናቸው ከቦታው እንደተነሳም አብራርተዋል። በእሁዱ ክስተት ከተገደሉት ውስጥ ሶስቱ በጅጋ ስላሴ ቤተክርስትያን እንደተቀበሩ መስማታቸውንም አክለዋል። “ከአሁን አሁን ወደ እኛም መጡ ስንል፤ የዝናብ መምጣት ነው የገላገለን። እንጂ እኛም አላቂ ነበርን” ሲሉ የአይን እማኙ በዕለቱ ያሳለፉትን “የጭንቅ ጊዜ” አስታውሰዋል።

“ከአሁን አሁን ወደ እኛም መጡ ስንል፤ የዝናብ መምጣት ነው የገላገለን። እንጂ እኛም አላቂ ነበርን”

በጅጋ ከተማ ያሉ የባጃጅ አሽከርካሪ

በጅጋ ከተማ በጉልበት ስራ እንደሚተዳደሩ የተናገሩ ሌላ የዓይን አማኝ፤ ለሰላማዊ ሰዎች ሞት መንስኤው “የፋኖ ኃይሎች በመከላከያ ላይ ትንኮሳ መፈጸማቸው ነው” ሲሉ ወቅሰዋል። በጎህ ሆቴል ውስጥ ተሸሽገው ማምለጣቸውን የሚናገሩት የዓይን እማኙ፤ በግድያው “18 ንጹሃን ተሰውተዋል። ሶስቱ ቁስለኛ ሆነዋል” ብለዋል። ከሟቾቹ ውስጥ “የመንግስት ሰራተኞች እና የባንክ ሰራተኞች” እንደሚበዙም አስረድተዋል።

የዓይን እማኙ ከትላንት በስቲያ እሁድ “በመከላከያ ኃይሎች” ተገድለዋል ከሚሏቸው መካከል፤ “በከተማው የምትታወቅ ዝናሽ የተባለች የአእምሮ ህመምተኛ” አንዷ ነች። በአእምሮ ህመምተኛዋ ላይ ተፈጸመ የተባለውን ግድያ፤ በጅጋ ጤና ጣቢያ የሚሰሩ አንድ የህክምና ባለሙያ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር አረጋግጠዋል። 

ከእሁዱ ግድያ በኋላ በጅጋ ከተማ ዝናብ መዝነቡ፤ “የሟቾችን አስክሬን ቶሎ ለማንሳት እንዳይችል” አድርጎት እንደነበር በጉልበት ስራ የሚተዳደሩት የከተማይቱ ነዋሪ ተናግረዋል። በከተማዋ መሃል የቆዩት “የመከላከያ ኃይሎች”፤ ምሽት አንድ ሰዓት ገደማ “ስታዲየም  እና ቁልቢጥ” በተባሉ አካባቢዎች ወደሚገኘው መኖሪያ ካምፓቸው ሲጓዙ መመልከታቸውን አክለዋል። 

አቶ አደራው የተባሉ ሌላ የከተማይቱ ነዋሪ፤ ጥቃቱ እና ግድያው ከተፈጸመ በኋላ በርካታ ወጣቶች ከከተማው ሸሽተው መውጣታቸውን ተናግረዋል። እርሳቸውም ለህይወታቸው በመስጋት ከጅጋ ከተማ ውጪ ባለ ቦታ ከቆዩ በኋላ፤ ዛሬ ማክሰኞ ጠዋት ወደ መኖሪያቸው መመለሳቸውን አመልክተዋል። 

ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ በጅጋ ጤና ጣቢያ የሚሰሩ የህክምና ባለሙያ፤ ከእሁዱ ክስተት በኋላ ቆስለው ወደ ጤና ጣቢያ የመጡ ሁለት ሰዎች መሞታቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። “ዓለሙ የሚባል ጸጉር ቤት የሚሰራ እና ኃይሉ ጥበቡ የሚባል ሰው፤ ህክምና ሳያገኙ ወዲያውኑ ህይወታቸው አልፏል” ያሉት እኚሁ የህክምና ባለሙያ፤ በእሁዱ ጥቃት በአጠቃላይ የሞቱ ሰዎችን ቁጥር እስካሁን በትክክል ማወቅ አለመቻላቸውን አስታውቀዋል።   

ቆስለው ወደ ጤና ጣቢያ ከመጡ ሰዎች መካከል፤ ዋሲሁን የሚባል አንድ ወጣት “አምስት ቦታ በጥይት ተመትቶ ነበር” ብለዋል። ይህ ወጣት “ከእነ ህይወቱ አድሮ”፤ በማግስቱ ቤተሰቦቹ ወደ ፍኖተ ሰላም ሆስፒታል እንደወሰዱትም አስታውሰዋል። ከቁስለኞቹ ውስጥ ሀብቱ ንጉስ የሚባል መምህር፤ በተመሳሳይ ሁኔታ ትላንት ጠዋት ወደ ፍኖተ ሰላም ሆስፒታል መላኩን ጠቁመዋል።

የእሁዱ ድርጊት የተፈጸመበት የጅጋ ምርጫ ክልል የፓርላማ ተወካይ የሆኑት አቶ አበባው ደሳለው፤ በዕለቱ በጅጋ ከተማ  “በመከላከያ ሰራዊት አባላት እና በፋኖዎች መካከል” የተኩስ ልውውጥ መካሄዱን ተከትሎ 13 ሰዎች መገደላቸውን እና ሁለት ነዋሪዎች መቁሰላቸውን አስታውቀዋል። የፓርላማ ተወካዩ ይህን ያስታወቁት፤ ለሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋማት እና ለመገናኛ ብዙሃን በዛሬው ዕለት ባሰራጩት መግለጫ ነው።

“ጓዶቻቸውን በሞት ያጡ የመከላከያ ሰራዊት አባላት፤ ጐህ ሆቴል ምግብ በመመገብ እና በመዝናናት በላይ የሚገኙ የባንክ ቤት ሰራተኞችና መምህራንን ወደ አስፓልት በማስወጣት አስበርክከው በጥይት በመደብደብ ገድለዋቸዋል። በተጨማሪም ከሞባይል ቤት መጠገኛ፣ ከጸጉር ቤት እና ከመኖሪያ ቤትም በማስወጣት ተጨማሪ ሰዎችን መግደላቸውን የአይን እማኞች ገልጸውልኛል” ሲሉ አቶ አበባው በመግለጫቸው ላይ አመልክተዋል።

የፓርላማ ተወካዩ በመግለጫቸው በስም ከዘረዘሯቸው ሟቾች መካከል፤ የጅጋ የአቢሲኒያ ባንክ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ዘመን አስማረ ይገኙበታል። የእዚሁ ባንክ ቅርንጫፍ ሌላ ተቀጣሪ እና የአዋሽ ባንክ ሰራተኛም እንዲሁ በዝርዝሩ ተካትተዋል። አቶ አበባው “ዘግናኝ” ሲሉ የጠሩት ግድያ፤ “መንግስት በተደጋጋሚ ስለሽግግር ፍትህና ስለ ሃገራዊ ምክክር በሚያነሳበት” ወቅት በመፈጸሙ “በእጅጉ ማዘናቸውንም” በመግለጫቸው ላይ አስፍረዋል።

“የመንግስት ኃይሎች ንጹሃንን መግደል በቀጠሉ ቁጥር [የአማራ] ክልል ሰላም እና ጸጥታ በእጅጉ እየተባባሰ የማያባራ ጦርነት ውስጥ እንደሚያስከትል ለማስገንዘብ እወዳለሁ” ያሉት የፓርላማ አባሉ፤ የመንግስት እና የፋኖ ተዋጊ ኃይሎች “ወደ እውነተኛ ድርድር እና ውይይት እንዲመጡ” ጥሪያቸውን አቅርበዋል። በንጹሃን ላይ የሚደርሰውን “ግድያ፣ ድብደባ፣ ንብረት ማውደም እና ሌሎች የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን” በተመለከተ፤ የሰብአዊ መብት ተቋማት የሙያቸውን ኃላፊነት “በአግባቡ በመወጣት ትብብር” እንዲያደርጉም ጠይቀዋል። 

የፓርላማ አባሉ መግለጫቸው እንዲደርሳቸው ካደረጓቸው የሰብአዊ መብት ተቋማት አንዱ ኢሰመኮ ነው። በኮሚሽኑ የሰብአዊ መብቶች ክትትልና ምርመራ ስራ ክፍል የሪጅን ዳይሬክተር ዶ/ር አለሙ ምህረቱ፤ ስለ እሁዱ ክስተት “መረጃው እንደደረሳቸው” ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። “ጥቃት ተፈጽሟል የሚል መረጃ አለ። ኦፊሰሮቻችን እየተከታተሉት ነው። ሆኖም አሁን ‘ሲቪሊያን’ ነው የተጎዱት? የግጭቱ ዓይነት ምንድነው? የሚለውን አጠቃላይ [ሁኔታውን] አላረጋገጥንም” ሲሉም አክለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር) 

Source: Link to the Post

Leave a Reply