You are currently viewing ‹በአማራ ክልል ግንደወይን ከተማ ተጠልለው ከሚገኙ ተፈናቃዮች መካከል አራት ወንድ አዛውንቶች እና አምስት ህጻናት አስፈላጊ የሆነ ሰብዓዊ እርዳታ ባለማግኘታቸው ምክንያት ህይወታቸው አልፏል›…

‹በአማራ ክልል ግንደወይን ከተማ ተጠልለው ከሚገኙ ተፈናቃዮች መካከል አራት ወንድ አዛውንቶች እና አምስት ህጻናት አስፈላጊ የሆነ ሰብዓዊ እርዳታ ባለማግኘታቸው ምክንያት ህይወታቸው አልፏል›…

‹በአማራ ክልል ግንደወይን ከተማ ተጠልለው ከሚገኙ ተፈናቃዮች መካከል አራት ወንድ አዛውንቶች እና አምስት ህጻናት አስፈላጊ የሆነ ሰብዓዊ እርዳታ ባለማግኘታቸው ምክንያት ህይወታቸው አልፏል› ኢሰመጉ የአማራ ሚዲያ ማዕከል መስከረም 12 2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ኢትዮጵያ ኢሰመጉ ያወጣው መግለጫ በተለያዩ አካባቢዎች እየተፈጸሙ ያሉ እስሮች፡ በሀገሪቱ በሚገኙ የተለያዩ ክፍሎች ውስጥ በዋናነት በአዲስ አበባ ከተማ በጋዜጠኞች፣ በማህበረሰብ አንቂዎች፣ በፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እና አባላት ላይ በተደጋጋሚ እስራት እየተፈጸመ ይገኛል፡፡ ኢሰመጉ ይህንን አስመልከቶ ድርጊቱ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን እና የፖለቲካ ምህዳሩ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚፈጥር ድርጊት በመሆኑ መንግስት ከእዚህ ተግባሩ እንዲቆጠብ በተደጋጋሚ ሲወተውት ቆይቷል፡፡ ሆኖም ግን እስራቱ ቀጥሏል ለዚህም ማሳያነት የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የድርጅት ጉዳይ ሀላፊ እና የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ስንታየሁ ቸኮል በኦሮሚያ ክልል ቡራዩ ፖሊስ ጣቢያ ታስረው የሚገኙ ሲሆን አቶ ስንታየሁ ጳጉሜ 5 ቀን 2014 ዓ.ም በ400 ብር ዋስ እንዲፈቱ ተወስኖ የነበረ ቢሆንም ፖሊስ በፍርድ ቤት ውሳኔ መሰረት ሊለቃቸው እንዳልቻለ እና በመጨረሻም ታስረውበት ከነበረው ፖሊስ ጣቢያ ወደ ቡራዩ ከተማ እንደተወሰዱ፣ መሰከረም 05 ቀን 2015 ዓ.ም በቡራዩ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንደቀረቡ እና በጊዜ ቀጠሮ ቡራዩ ፖሊስ ጣቢያ ታስረው እንደሚገኙ ኢሰመጉ ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለመረዳት ችሏል፡፡ ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ እና ጋዜጠኛ መአዛ መሀመድ ከዚህ ቀደም በፖሊስ ተይዘው በእስር ላይ የቆዩ መሆኑን እና በዋስ መለቀቃቸው የሚታወስ ሲሆን በድጋሚ ጳጉሜ 02 ቀን 2014 ዓ.ም በፖሊሶች መታሰራቸውን እና ጳጉሜ 04 ቀን 2014 ዓ.ም እና መስከረም 06 ቀን 2015 ዓ.ም ፍርድ ቤት በቀጠሮ መቅረባቸውን በነዚህም ጊዜያት ፌደራል ፖሊስ የምርመራ ጊዜ የሚጠይቀው መረጃ ለማሰባሰብ በሚል እንደሆነ ኢሰመጉ ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለመረዳት ችሏል፡፡ በተመሳሳይ ጋዜጠኛ አባይ ዘውዱ ጻጉሜ 05 ቀን 2014 ዓ.ም መታሰሩን፣ መስከረም 05 ቀን 2015 ዓ.ም በዋለ ችሎት በ5000 ብር ዋስ እዲለቀቅ ተወስኖ የነበረ ቢሆንም የፌደራል ፖሊስ ይግባኝ ጠይቃለው በሚል ጋዜጠኛውን እንዳልለቀቀው ኢሰመጉ መረዳት ችሏል፡፡ ኢሰመጉ በደረሰው ጥቆማ መሰረት መስከረም 04 ቀን 2015 ዓ.ም በፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ በአካል በመገኘት በእስር ላይ የሚገኙትን ጋዜጠኞች አያያዝ ሁኔታ ለመመልከት ያደረገው ሙከራ የፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ሊሳካ አልቻለም፡ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ሁኔታ ከተለያዩ አካባቢዎች በግጭቶች ምክንየት ተፈናቅለው በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ውስጥ ተጠልለው የሚገኙ ተፈናቃዮች የሚደረግላቸው ሰብዓዊ እርዳታ እጅጉን አነስተኛ መሆኑን እና በክልሉ በሚገኙ አንዳንድ አካባቢዎች ተጠልለው የሚገኙ ተፈናቃዮች ደግሞ ምንም አይነት ሰብዓዊ እርዳታ እያገኙ አለመሆኑን ኢሰመጉ ከአካባቢዎቹ እና ከተፈናቃዮች ባገኘው መረጃ ለመረዳት ችሏል፡፡ ለዚህም ማሳያነት ከምስራቅ ወለጋ ዞን እና ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሽ ዞን በነበረ ግጭት ተፈናቅለው በአማራ ክልል ግንደወይን ከተማ ተጠልለው ከሚገኙ ተፈናቃዮች መካከል አራት ወንድ አዛውንቶች እና አምስት ህጻናት አስፈላጊ የሆነ ሰብዓዊ እርዳታ ባለማግኘታቸው ምክንያት ህይወታቸው አልፏል፣ ከምስራቅ ወለጋ ዞን በግጭት ምክንያት ተፈናቅለው በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞን መርጦ ለማሪያም ከተማ ውስጥ ተጠልለው ከሚገኙ ተፈናቃዮች መካከል ስድስት ሰዎች (ሶስት ሴት እና ሶስት ወንድ) ሰብዓዊ እርዳታ ባለማግኘታቸው ምክንያት በረሀብ ህይወታቸው ማለፉን እና ከነዚህም መካከል አራቱ ህጻናት መሆናቸውን ኢሰመጉ ከተፈናቃዮች ባገኘው መረጃ ለመረዳት ችሏል፡፡ በተጨማሪም በሰኔ 11 ቀን በኦሮሚያ ክልል ወለጋ ቶሌ ቆሉ ወረዳ የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ ከአካባቢው ተፈናቅለው በአማራ ክልል በሀርቡ ከተማ ተጠልለው የሚገኙ 5560 ተፈናቃዮች መኖራቸውን እና እነዚህ ተፈናቃዮች ከመንግስት የሚደረግላቸው ሰብዓዊ እርዳታ ባለመኖሩ ምክንያት የምግብ እና የውሀ እጥረት እንዳጋጠማቸው ይህንንም ተከትሎ ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሚገኙ ኢሰመጉ ከተፈናቃዮች ባገኘው መረጃ መሰረት ለመረዳት ችሏል፡፡ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ጉራጌ ዞን የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች፡ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ጉራጌ ዞን ምክር ቤት ዞኑ ከአጎራባች ዞኖች እና ልዩ ወረዳ ጋር አንድ ላይ በክልል እንዲደራጅ በመንግስት የቀረበውን ሀሳብ ውድቅ አድርጎ እንደነበር፣ ዞኑ በኮማንድ ፖስት ስር እንደሆነ፣ የክልል አደረጃጀት ጥያቄን ተከትሎ ከነሀሴ 14 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ሰባት አመራሮች እና አስራ ሁለት ወጣቶች አንደታሰሩ እና በመስከረም 10 አና 11 ቀን 2014 ዓ.ም የታሰሩት ሰዎች በሙሉ መለቀቃቸውን ኢሰመጉ ከአካባቢው ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለመረዳት ችሏል፡ በኦሮሚያ ክልል የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች፡ በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ ሰፍሮ የነበረው የመከላከያ ሰራዊት የሰሜን ኢትዮጵያውን የትጥቅ ግጭት ዳግም መቀስቀሱን ተከትሎ አካባቢውን ለቆ በመውጣቱ ምክንያት አንዳንድ አስቀድሞ የጸጥታ ስጋት የነበረባቸው አካባቢዎች በሸኔ ታጣቂ ቡድን በመያዛቸው ምክንያት በአካባቢው የሚገኙ ነዋሪዎች ላይ ግድያ፣ ዝርፊያ እና አፈና እየተፈጸመ ይገኛል፡፡ ቀድሞ ሰላም የነበሩ እንደ ኢሉ አባቦራ እና ቡኖ በደሌ ዞን ወረዳዎች በታጣቂ ቡድኑ ጥቃት እየተፈጸመ በሰው ህይወት እና ንብረት ላይ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን ኢሰመጉ ከአካባቢው ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለመረዳት ችሏል፡፡ በእነዚህ ዞኖች በታጣቂ ቡድኑ በተከፈቱ ጥቃቶች ቁጥራቸው በግልጽ ያልታወቁ ሰዎች መሞታቸውን እና በአካባቢው የሚገኙ ባንክ ቤቶች መዘረፋቸውን፣ በሸኔ ታጣቂ ቡድን እና በመንግስት የጸጥታ አካላት መካከል በሚደረግ የተኩስ ልውውጥ ምክንያትም እየሞቱ የሚገኙ ሲቪል ሰዎች መኖራውን ኢሰመጉ ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለመረዳት ችሏል፡፡ በተመሳሳይ በክልሉ በሚገኙ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ በዋናነት ጉዳቱ አርጆ በሚባል አካባቢ እና በነቀምቴ ከተማ በመንግስት የጸጥታ አካላት ሀገወጥ እስሮች እየተፈጸሙ መሆኑን ኢሰመጉ ከአካባቢዎቹ ከደረሱት መረጃዎች ለማረጋገጥ ችሏል፡፡ በተጨማሪም በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ጃርዴጋ ጃርቴ ወረዳ ላይ ከፍተኛ የሆነ ጥቃት በታጠቁ ቡድኖች መስከረም 12 ቀን 2014 ዓ.ም ከጠዋት ጀምሮ እየተፈጸመ መሆኑን እና በዚህም ጥቃት በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች እየተገደሉ መሆኑን፣ መሰል ድርጊቶች የሰሜን ኢትዮጵያው የትጥቅ ግጭት ዳግም መቀስቀሱን ተከትሎ የመከላከያ ሰራዊት አካባቢውን ለቅቆ በመውጣቱ እና ትኩረት እየተሰጠው ባለመሆኑ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች እየተፈጸመ መሆኑን ኢሰመጉ ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለመረዳት ችሏል፡፡ በአማራ ክልል የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች፡ በአማራ ክልል በባህርዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት ሀላፊ ኮማንደር ዋጋው ታረቀኝ መስከረም 11 ቀን 2014 ዓ.ም አመሻሽ ላይ በጥይት ተመተው መገደላቸውን እንዲሁም ከዚህ ቀደም የሸዋሮቢት ከተማ አስተዳደር የሆኑት አቶ ውብሸት አያሌው በጥይት ተመተው መገደላቸው አረጋግጠናል፡፡ የኢሰመጉ ጥሪ፡ • መንግስት በጋዜጠኞች፣ በማህበረሰብ አንቂዎች፣ በፖለቲካ ፓርቲ አባላት እና አመራሮች ላይ እየፈጸመ ያለው እስር ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት እና የፖለቲካ ምህዳሩ ላይ ከፍተኛ አደጋ የሚጥል በመሆኑ ከዚህ ድርጊቱ እንዲቆጠብ፣ • በተለያዩ አካባቢዎች ታስረው በፍርድ ቤት ጉዳያቸውን እየተከታተሉ ያሉ ጋዜጠኞች፣ የማህበረሰብ አንቂዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት እና አመራሮች አፋጣኝ ፍትህ (The right to speedy trials) የማግኘት መብታቸውን እንዲያከብር እና አላግባብ ጉዳያቸውን እንዳያራዝም፣ • ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስተዋለ የመጣው በፖሊስ የፍርድ ቤት ውሳኔን አለማክበር ጉዳይ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት የፍርድ ቤት ውሳኔን ወደጎን በመተው ሰዎችን አላግባብ የአካል ነጻነታቸውን በሚጋፋ መልኩ የሚይዙ አካላት ላይ ህጋዊ ተጠያቂነትን እንዲያደርግ፣ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተፈናቃዮች በመኖራቸው እንዲሁም በግንደወይን እና በመርጦ ለማርያም መጠለያ ጣቢያዎች ለሚገኙ ተፈናቃዮች መንግስት እና መንግስታዊ ያልሆኑ የሰብዓዊ ድጋፍ የሚያደርጉ አለም አቀፍ እና ሀገር አቀፍ ድርጅቶችለእነዚህ ተፈናቃዮች ተገቢውን ሰብዓዊ እርዳታ በአስቸኳይ እንዲያቀርቡ፤ • በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ወስጥ በግንደወይን እና በመርጦ ለማርያም መጠለያ ጣቢያዎች ከሚገኙ ተፈናቃዮች መካከል በምግብ እጥረት ምክንያት የንጹሃን ህይወት እንዲያልፍ ምክንያት የሆኑ አካላት ተጠያቂ እንዲደረጉ፤ • መንግስት በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ውስጥ በሚገኙ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ በሸኔ ታጣቂ ቡድን የሚደርሱ ጥቃቶችን በአስቸኳይ እንዲያስቆም፣ እየደረሱ ያሉ ጥቃቶችንም እንዲሁ እንዲያስቆም እና የአካባቢዎቹን ሰላም እንዲያረጋግጥ እና በአካባቢው ስልጣንን አላግባብ በመጠቀም በመንግስት የጸጥታ አካላት የሚደረጉ እስሮችን እንዲያስቆም፣ • ኢሰመጉ በተለያዩ ጊዜያት በአማራም ሆነ በሌሎች ክልሎች በንጹሃንና በፀጥታ ሀይሎች ላይ ጭምር እየተደረገ ያለውን ግድያ እያወገዘ ድርጊቱን የፈጸሙ አካላትን መንግስት ተጠያቂ እንዲያደርግ እንዲሁም በዘላቂነት ማህበረሰቡ ደህንነት ተሰምቶት መንቀሳቀስ ይችል ዘንድ በአካባቢው ሰላማዊ ሁኔታ እንዲኖር እንዲያደርግ፤ • መንግስት በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ጉራጌ ዞን የክልል አደረጃጀት ጥያቄን ተከትሎ እየደረሱ ያሉ እስሮችን በማስቆም ጥያቄወዎች በሰላማዊ መንገድ የሚፈቱበትን ሁኔታ እንዲያመቻች እና ህዝቡም ጥያቄውን እንደከዚህ ቀደሙ በሰላማዊ መንገድ እንዲያቀርብ ኢሰመጉ ጥሪውን ያቀረባል፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply